የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የማዕከላዊ ኮሚቴ በባሕርዳር ከተማ ባደረገው አስቸኳይ ጉባዔ ከድርጅታዊ ሪፎርምና የጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን አሳለፈ።

83
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መጋቢት 2/2015 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አድርጓል። በዚህም በቀዳሚ አጀንዳነት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመካከሉ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት የተከሰተውንና ተቋሙ የተጣለበትን ሕዝባዊ ኀላፊነት በሙሉ አቅሙ እንዳይወጣ ያደረገውን ማነቆ በውይይት እልባት የሰጠበትን፣ ብሎም ለተፈጠረውም ችግር አባላትና ደጋፊዎቹን ይፋዊ ይቅርታ የጠየቀበትን ሂደት፣ ለድርጅቱ ቀጣይ ህልውና ካለው አወንታዊ አስተዋፅኦ አኳያ ተወያይቶ እውቅና ሰጥቷል።
በተጨማሪም ንቅናቄው ያልተጠናቀቁ የጉባዔ ዝግጅት ተግባራትን በመገምገም፣ ድርጅቱ ታድሶና ተጠናክሮ ለመውጣት የሚያስችለውን ጉባዔ በአጭር ጊዜ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ በስፋት በመወያየት የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፦
1ኛ ከዚህ ቀደም በጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ኮሚቴ በኩል የተሠሩ ሥራዎችን፣ በሂደቱ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በጥልቀት በመገምገም ብሎም የተጓደሉ የኮሚቴው አባላትን በማሟላት፣ ኮሚቴው ቀሪ ተግባራትን አጠናቅቆና እንዲስተካከሉ ሀሳብ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች አስተካክሎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማእከላዊ ኮሚቴ እንዲያቀርብ ወስኗል፡፡
May be an image of 13 people, people standing and indoor
2ኛ ልዩነቶችን ፈትቶ በአዲስ መንፈስ የተነሳው የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት እንዲያሳልጥ የስራ መመሪያ በመስጠት፣ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የተቋቋሙት ልዩ ልዩ የሥራ ቡድኖችን እንዲከታተል፣ የሎጅስቲክና ሌሎች ለሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንዲያሟላ፣ ብሎም የፋይናንስ ግብረ-ኀይል አቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እንዲመራ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
3ኛ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ማከናወኛ ጊዜና ቦታን በተመለከተ አስቻይና ፈታኝ ሁኔታዎችን በመገምገም፣ ጠቅላላ ጉባኤው ከግንቦት 5-6/2015 ዓ.ም እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
4ኛ ወቅታዊ የሀገራችንና የሕዝባችን ሁኔታዎችን በተመለከተም፦ የንቅናቄው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት በመገምገም፣ የድርጅቱን አቋም ለሕዝብ በይፋዊ መግለጫ እንዲያሳውቅ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀደም ሲል በድርጅቱ ውስጥ ለታየው በሙሉ አቅም ያለመስራት ችግርና ተያያዥ ጉዳዮች ኃላፊነቱን በመውሰድ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚኖሩ መላው የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኘው የአማራ ሕዝብ ይፋዊ ይቅርታ ይጠይቃል።
በመጨረሻም ማዕከላዊ ኮሚቴው መላው የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎቹ፣ አብን ከትናንትናው በተሻለ መልኩ የህዝባችን አታጋይ ድርጅት ሆኖ መቀጠሉ አማራጭ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ፣ ንቅናቄው ለሚያደርገው የጠቅላላ ጉባኤና አጠቃላይ ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች የተለመደ ድጋፍና አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን በማስተላለፍ ጉባዔውን አጠናቅቋል፡፡
መረጃው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!