የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘር ማጥፋት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፡፡

841
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘር ማጥፋት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ህዝብ ለሶስት አስርተ ዓመታት በጠላትነት ፈርጆ ዘርፈ ብዙ ስርዓታዊና መዋቅራዊ ግፍ ሲፈፅምበትና ሲያስፈፅምበት የቆየውን የትህነግ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል፡፡ ትህነግ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደትና አረመኔያዊ ግፍ በመፈፀም አገሪቱን ለመበታተን ያደረገውን ሙከራ ለማክሸፍ የአማራ ህዝብ ከፍተኛ ትግል እንዳደረገ አብን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የአማራ ህዝብ ቅን ልቦናና ታግሽነት እንዲሁም የከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጡና ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትህ የሚኖርባትን አገር ለመገንባት ያነገበዉን ተስፋ ለማምከን እኩያን በጥምረት የተቀናጀ ጥቃት ከፍተውበታል ብሏል፡፡ የአማራ ህዝብ ሲፈጸሙበት ከቆዩት ሰፊ ዘር ተኮር ጥቃቶች ገና ባላገገመበት ሁኔታ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በአማራ ጠልነት መንፈስ ስልታዊ የዘር ማፅዳትና የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴዎች በአዲስ መልክ ተጠናክረዉ እየታዩ መሆኑን ተገንዝበናል ብሏል አብን በመግለጫው፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ወጀለኞችን ለማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍን ለማከናወን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ትሕነግን ከሞት መንጋጋ ፈልቅቆ ለማውጣት፤ ይህ ካልተሳካም የአፍራሽነትና የጥላቻ አጀንዳውን ለማስቀጠል በቅንጅት የተሰለፉ ኃይሎች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሰብዓዊ ቀውስ ማዕከል አድርገውታል ነው ያለው፡፡
በዚህ ጥቃት እየተሳተፉ ያሉ ጽንፈኛና የጥላቻ ኃይሎች በመካከላቸው መሰረታዊ የሆኑ የግብ ልዩነቶች ቢኖሯቸዉም በአማራ ህዝብ ላይ ያነገቡት የጥላቻና የጥፋት ፖለቲካ በጋራ እንዳሰለፋቸው ይታወቃል ብሏል፡፡ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል መነሻ ምክንያቶቹ ትሕነግ በሕዝባችን ላይ በቀጥታ እንዲሁም በትርክት፣ በፖሊሲ፣ በመዋቅር፣ በሎጅስቲክስና በገንዘብ እገዛ እያደረገ ሲያስፈጽም መቆየቱ፤ መነሻዉ ጽንፈኞች በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸው ጥላቻ ሲሆን በዋናነት ሕዝቡን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳት የታለመ መሆኑን፤ ትሕነግ በጥላቻ፣ በአግላይነትና በአምባገነንነት የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን በኃይል ወደ ትግራይ በማካለል፤ ሌሎች የአማራ አካባቢዎችን ደግሞ በሕገ-ወጥና በማንአለብኝነት ወደ ተለያዩ ክልሎች አካቷቸው እንደነበር አብን አመላክቷል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ የሚኖረው የአማራ ህዝብ በሁሉም ዘርፎች የሚገለጹ ሰብዓዊ መብቶቹን ተገፎ፤ በተለይም አጠቃላይ ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቆ መቆየቱንና በመተከል የሚኖረውን የአማራ ህዝብ የመብት ጥያቄ ለማዳፈን ሰፊና የተቀናጀ ሴራ እየተተገበረ መሆኑን፤ እስካሁን በሕዝቡ ላይ በርካታ ተደራራቢ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን ለመከላከልም ይሁን ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አገራዊና መንግስታዊ ትጋት አለመኖሩ ገልጿል፡፡
በመንግስት መዋቅር ውስጥ በየእርከኑ የኃላፊነት ቦታዎችን የያዙ አመራሮችና ባለስልጣናት ጥቃት ለሚሰነዝሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ከለላ በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ ጭምር ከፍተኛ የአፍራሽነት ድርሻ እንዳለቸው አብን ገልጿል፡፡ ዛሬም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን የአገሩን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘውን ድል ለመንጠቅ፣ አመድ አፋሽ ለማድረግና ሕዝቡን በጠላትነት ፈርጆ ለመቀጠል የሚፈልጉ ኃይሎች ከሚከተሉት የሕዝብ አገት ፖለቲካ (hostage politics) ያልታቀቡ መሆኑን መረዳት ይገባል ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና በሕዝቡ ራስን የመከላከልና አገርን የመታደግ ዘመቻ የተንበረከከው የትሕነግ ኃይል ታሪካዊና ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም ከሞት በኃላ ቋሚ ማሳበቢያ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቅሷል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ዘግናኝና አረመኔያዊ ድርጊቶች ኮማንድ ፖስት በመመስረቱ ሊሻሻል ይችላል ብለን የጠበቅነው ዘር ተኮር ጥቃት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
አብን ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የተሰራውን ርዕዮታዊ፣ሕጋዊና መዋቅራዊ የጥላቻና የጭቆና ሥርዓት ከናካቴው ለማስወገድና ሕዝቡ ኅልውናው ተከብሮ እንዲኖር ለማስቻል ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአማራዊ ማንነት ላይ ያነጣጠረዉን ጥቃት ለመከላከልና በዘላቂነት ለመቀልበስ መላዉ የአማራ ሕዝብ፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ሁሉም የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች የማያወላዳ የጋራ አቋም መውሰድና ተፈጻሚነት ያለው የፖለቲካና የደኅንነት እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ አብን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here