“የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ይበልጥ ወደ ሕዝብ እየቀረበ ለማገልገል አደረጃጀቱን እና አሠራሩን እያሻሻለ ይገኛል” የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ

0
36
“የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ይበልጥ ወደ ሕዝብ እየቀረበ ለማገልገል አደረጃጀቱን እና አሠራሩን እያሻሻለ ይገኛል” የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ሥርጭት ማስጀመሪያ መርኃግብር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥርጭት ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚገኝ በመርሃ ግብሩ ተገልጿል፡፡ በመርኃግብሩ ላይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት የቀድሞው አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የአሁኑ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከ26 ዓመታት በፊት በውስን ሃብት እና በትንሽ የሰው ኃይል የሚዲያ አገልግሎቱን የጀመረ፣ በየጊዜው እያደገ፣ እየተቀየረ እና ሙያውን እያሳደገ የመጣ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡
ሚዲያው በትንሽ ደረጃ ሥራውን ጀምሮ በየዓመታቱ ለውጥ እያመጣና በየጊዜው ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር እየተራመደ ዘርፍ ብዙ እድገቶችን እያሳየ የሚገኝ የሕዝብ ሚዲያ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በ6 ቋንቋዎች ማለትም (በአማርኛ፣ አዊኛ፣ ኽምጣና፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች) ዜና፣ ፕሮግራም እና መጣጥፍ በማቅረብ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በራዲዮ፣ በጋዜጣ እና በቴሌቪዥን እንዲሁም በአዲሱ የሚዲያ አውታር (ኦንላይን) ጭምር በሀገር ውስጥና በውጭ፣ በከተማና በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ ለማገልገል ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ ለመሆን እየተጋ እንደሚገኝ ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል፡፡
የራዲዮ ስርጭት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለውን በገጠር የሚኖረውን ኅብረሰተብ የሚዲያ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዛሬ ስርጭት እየጀመረ ያለውን የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 ጨምሮ 6 የራዲዮ ጣቢዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ፤ የማቀባበያና ሌሎች ቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከ8 በላይ የራዲዮ ማሰራጫዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ተደራሽነትን ለማስፋት የሰቆጣ ኤፍ ኤም እና የአዲስ አባባ ተጨማሪ የኤፍ ኤም ጣቢያዎችን ሥራ ለማስጀመር ኮርፖሬሽኑ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሚነሳውን የዘገባ ፍትሐዊነት ጥያቄ ለመቅረፍ በርካታ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ያሉት ሥራ አስፈጻሚው የቅርንጫፍ ጣቢያዎች በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ እየተሟሉ እንዲሄዱ እና የቴሌቪዥን ዘገባ መሥራት እንዲችሉ መደረጉ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል። በሌሎች ያልተሟላባቸው አካባቢዎችም ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
“የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ይበልጥ ወደ ሕዝብ እየቀረበ ለማገልገል አደረጃጀቱን እና አሠራሩን እያሻሻለ ይገኛል” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡ በደሴ ከተማ ዘመናዊ የሚዲያ አገልግሎት መስጠት የሚችል የሚዲያ ህንጻ ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል፡፡
የጎንደር ኤፍ ኤም 105.1 የጎንደር ከተማ እና አካባቢው ሕዝብ የሚሳተፍበት፣ እውነትና እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ያለው ከሕዝብ በመሆኑ እንድትጠቀሙበት በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የጎንደር ኤፍ ኤም 105.1 እና ሌሎች የማስፋፊያ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሙሉቀን ሰጥዬ
ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here