የአማራ ሚደያ ኮርፖሬሽን የሚዲያ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሠራ ነው።

0
41

የአማራ ሚደያ ኮርፖሬሽን የሚዲያ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሠራ ነው።

የጎንደር እና የደብረ ማርቆስ ኤፍ ኤም ስርጭትን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል።

በቀጣይ ዓመታት ሁሉም ዞኖች የራዲዮ ጣቢያ እንዲኖራቸው ተቋሙ አቅዶ እየሠራ ነው።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የክልሉ ልሳን መሆን የጀመረው ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በስምንት ገጾችና በ4 ሺህ ቅጂ ታትማ በምትሰራጨው የበኩር ጋዜጣ አማካኝነት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ‹የአማራ ክልል ድምጽ የሬዲዮ ጣቢያ› ስርጭት ተጀምሯል፣ ከሚያዚያ 19/1992 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የ30 ደቂቃ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ዝግጅት ሽፋን ተጀመረ፡፡

በሀገሪቱ በ1994 ዓ.ም ኤፍኤም ጣቢያ በማቋቋም ሁለተኛ የሆነበትን ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9 ዕለታዊ ስርጭት አስጀምሯል፤ በመቀጠልም በክልሉ መንግሥት ሙሉ ወጪ ደብረ ብርሃን እና ደሴ ከተሞች የኤፍ ኤም ማሰራጫ ጣቢያዎችን አስገንብቶ መደበኛ ስርጭት እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት አሚኮ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ዝግጅት፣ የ18 ሰዓት አጭርና መካከለኛ ሞገድ የሬዲዮ ስርጭት፣ በጋዜጣና በአዲሱ የመገናኛ ዘዴ (ኦንላይን) አማራጮች ወደ ሕዝብ እየደረሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ ለብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል ዕድገትም ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል። ከአማርኛ በተጨማሪ በኽምጣና፣ በኦሮምኛ፣ በአዊኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተደራሽ የነበረው አሚኮ አሁን ደግሞ በትግረኛ ቋንቋ ለታዳሚያን መድረስ ጀምሯል፣ በቅርቡም በሌሎች የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎች ስርጭት ለመጀመር እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከ26 ዓመታት በላይ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በዘገባ ጥራትና በሌሎችም ዘርፎች ባስመዘገባቸው ሁለንተናዊ እድገቶች በሀገሪቱ የብዙኀን መገናኛ ታሪክ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል አቶ ሙሉቀን፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በመግለጫቸው የሚዲያውን ተደራሽነት የማስፋትና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሁሉም ዘርፎች እየተሻሻለ የመጣው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት የሕዝብን ፍላጎትና የተዘጋጀውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት በማድረግ በርካታ የማሻሻና የማስፋፊያ ሥራዎችን ሠርቷል፤ ከማሻሻያዎቹ መካከል ተቋሙ የደረሰበትን የአገልግሎት ደረጃና የቴክኖሎጂ አቅም ታሳቢ በማድረግ ከብዙኀን መገናኛ ድርጅትነት ወደ ሚዲያ ኮርፖሬሽንነት እንዲያድግ መደረጉ ዐቢይ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ይህም የሙያ መርሕን አክብሮ የሚሠራ የሚዲያ ተቋም እንዲሆን፤ የሕግ ከለላ እንዲኖረው፤ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች መረጃ መስጠት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያደርግ እና ጋዜጠኞች በገለልተኝነት፣ በነጻነትና በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሠሩ የሚያበረታታ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

ፍትሐዊ የዘገባ ሽፋን ለመስጠትና ተደራሽነትን ለማስፋት ቅርንጫፎችን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው፤ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ወልዲያ የቴሌቪዢን ዘጋቢዎች ቡድን በማዋቀር አካባቢዎቹ ሽፋን እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል፤ በአዲስ አበባም ስቱዱዮ ተገንብቶ ሀገራዊ ጉዳዮች ሽፋን እየተሰጣቸው ነው፤ ይህንን ማጠናከር የቀጣይ ተግባር መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ ሙሉቀን ሰጥዬ ያስገነዘቡት፡፡

በተለይ የሬድዮ ተደራሽነትን ለማስፋት ከባሕር ዳር፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከየሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች በማቀባበያ ቴክኖሎጂ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስርጭቱን የበለጠ ለማስፋት ደብረማርቆስና ጎንደር የሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች ተገንብተዋል፤ በሙከራ ስርጭት ላይ የሚገኙት ጣቢዎቹ የሰው ኀይል ተሟልቶላቸው ዝግጁ ሆነዋል፤ በሚቀጥሉት ቀናት ቀጥታ ስርጭት የሚጀምሩ ሲሆን የስድስት ሰዓት ዕለታዊ የአየር ሽፋንም ይሰጣሉ ነው ያሉት፡፡

የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 እና አማራ ኤፍ ኤም ደብረማርቆስ 95.1 መደበኛ ስርጭት መጀመር የኮርፖሬሽኑን ተደራሽነት እንደሚያሳድግ የተናገሩት አቶ ሙሉቀን ይሁን እንጂ ሁለቱ ጣቢያዎች ሥራ ከጀመሩ በኋላም ተደራሽ የማይሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ፤ እነዚህን አካባቢዎች የማቀባበያ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ሽፋን ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሰቆጣ ላይም በአማርኛና በኽምጣና አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ እየተገነባ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሬዲዮ ስርጭት ይጀምራል፤ ይህም የአማራ ሕዝብን የኑሮ ሁኔታ፣ ባሕል፣ እሴትና ትክክለኛ ማንነት ለከተማዋና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በማስገንዘብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

የሰቆጣና የአዲስ አበባ የሬዲዮ ጣቢያዎች መደበኛ ስርጭት ሲጀምሩ አሚኮ ስምንት የቀጥታ ስርጭት የሬዲዮ ጣቢያዎች ይኖሩታል፡፡ በምሥራቅ አማራ ሁለት የሬዲዮ ጣቢያዎችና በርከት ያሉ የማቀባበያ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም ተደራሽ ያልሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በደሴ ከተማ ሁሉን አቀፍ የሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ባለ 11 ወለል ህንጻ ሊገነባ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የግንባታው ዲዛይን የተጠናቀቀ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት የግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደሚኖር አቶ ሙሉቀን አመላክተዋል፡፡ ይሕም በቀጣናው ያለውን የሚዲያ ተደራሽነት ችግር የሚፈታ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳስታወቁት በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ሁሉም ዞኖች የሬዲዮ ጣቢያ እንዲኖራቸው ታስቧል፡፡ የተቋሙን አቅምና የክልሉን መንግሥት ድጋፍ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ እየተሰጠ እቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

ሚዲያው የበለጠ እንዲያድግ የሚመለከታቸውና አጋር አካላት ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ሙሉቀን ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ሚዲያውን ለማሳደግ የሚያግዙ ገንቢ ሀሳብና አስተያየት መስጠት፣ ማደግ የሚችልባቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮች በማሳየትና በይዘት ቀረጻ ማሻሻያ ግባት በመስጠት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ:– ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here