“የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶቹን ለማሳካት እንደ መሪ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል እንገባለን” የአማራ ክልል መሪዎች

537

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ኮንፈረንስ ለቀናት በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር ቆይቶ ተጠናቅቋል። የመሪዎች ኮንፈረንስ ለቀናት ከመከረ በኋላ ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው የተጠናቀቀው።

በአቋም መግለጫው ባለፉት ዓመታት በውጤታማ ድሎችን ማስመዝገቡን አንስቷል፡፡ የተገኙት ድሎች በፈተና የተሞሉ እንደበሩም አስታውቋል፡፡ ስኬቶችን በማጽናት አሁናዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ለመሄድ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት የምንቆምበትና የትግል መስመራችንን የምናጸናበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብሏል፡፡ የገጠሙንን ችግሮች ከመሠረታቸው ለመፍታት የሚያስችሉ የአስተሳሰብና የተግባር መፍትሔዎችን ማጎልበት የምንችልበትን ስልቶች የጋራ አድርገናልም ነው ያለው፡፡

የአማራ ክልል አሁን ላይ የሚገኝበትን ፖለቲካዊ ችግሮች ፈር ለማስያዝ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን ተጣብተው የተፈጠሩ አደጋዎችን ለመቀልበስ ሁሉንም አይነት ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ያለሰለሰ ፖለቲካዊ ትግል እየተደረገ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ፍትሐዊነታቸውና ተገቢነታቸው የማያወላዳ ነው ያለው መግለጫው መሠረታዊ ጥያቄዎችን በጸረ ኢትዮጵያ እና ጸረ አማራ አቋም ህልውናቸውን በመሠረቱ ቡድኖች በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ ላይ በተመሠረተ የፖለቲካ ፍላጎቶች ተጣምመው የተቀነበቡ በመሆናቸው የትግሉን ዳርቻ እልህ አስጨራሽና የረዘመ ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል ነው ያለው፡፡ በሕዝባችን ማንነት ላይ ያነጣጠሩ መርዘኛ የፖለቲካ የጥላቻ ውትወታዎችን እንደ ትግል ስልት የሚጠቀሙና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያቀነጭር የሕግ ድንጋጌዎች፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ አሥተዳደራዊ አደረጃጀት ከአንድ ትውልድ እድሜ በላይ ሲተገበር የቆየ መሆኑ አሁናዊ የአማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ ችግር ሥር የሰደደና የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታልም ብሏል፡፡

የሕዝባችን ጥያቄዎች አወንታዊ ምላሽ እንዲያገኙ ለጋራ ዓላማ ውስጣዊ አንድነትን ከማጽናት ባሻገር የኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍን ያስቀደመ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር የላቀ መተማመን እና መተባበርን መፍጠር ይገባልም ነው ያለው፡፡

የመሪዎቹ ኮንፈረንስ የክልሉን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውስጣዊ ውይይት ማድረጉንም አመላክቷል፡፡ የካበተ ሥርዓተ መንግሥት ምሥረታ ልምድ ያለው ሕዝብ አካል ነን ያለው መግለጫው የዛሬያችን መሠረት የሆነውን ትናንታችን በምልሰት በመቃኘት፣ ለነጋችን ፍካት ጉልበት የሚሆንበትን እድል እንደ ወረት ለመውሰድና ሕጸጾችን እያረሙ የጋራ ቅቡልነት የተቸረው መንግሥት ለመገንባት በሚያስችል ሕብረ ብሔራዊ ሂደት ላይ ትኩረት የመስጠት አማራጭን አስቀድመናልም ብሏል። ያጋጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን የምናሻግርበትን አቅጣጫዎችን ለይተናልም ብሏል በመግለጫው፡፡

በአቋም መግለጫው ብሔር ላይ በተመሠረተ የፌደራል አወቃቀር በሕዝቦች አንድነት ሳይሆን እርስ በእርስ የመጠራጠር እና የመከፋፈል አዝማማያ እንዲፈጠር ሆን ተብሎ ስሁት የሆነ የፖለቲካ ትርክት በመፈጠሩ የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያጣ እና የግጭትና የመፈናቀል ሰላባ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያለው፡፡ የሕዝቡን ትግልና የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ ሪፎርም መደረጉንም አስታውቋል፡፡ የብሔር አስተሳሰብን ከሀገራዊ አስተሳሰብ ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ጊዜ ይጠይቃል ያለው መግለጫው ሂደቱን ዳር ለማድረስና ወንድማማችነትን እና እህታማማችነትን ለማጽናት ቃል እንገባልንም ብሏል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በቀጥተኛም ኾነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች ፈጥኖ ለማከም ሁለንተናዊ አቅሞችን በማቀናጀት ሕዝቡ ከጉዳቱ ፈጥኖ እንዲወጣ እንዲያገግምና ተወዳደሪ ክልል ለመገንባት ያለ እረፍት እንደሚሠራም አረጋግጧል፡፡ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ አማራጮች ለመፍታት ቀዳሚ አማራጭ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው ሌሎች ኃይሎችም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በኮንፈረንሱ ስኬቶችን፣ ፈተናዎችን እና የመውጫ ስልቶችን በሚገባ መገንዘብ መቻሉንም አስታውቋል፡፡ ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን እውነተኛ ሰላም፣ የዲሞክራሲና የመልማት ፍላጎት እንዲሳካ የክልሉ መሪዎች ሌት ተቀን ለመሥራት እና ሁሉንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለንም ብሏል በመግለጫው፡፡

የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ወቅታዊ ችግሮች እንዲፈቱ በጋራ እየመከረ የጋራ መፍትሔዎችን እያስቀደመ ችግሮችን ለመፍታት ሙሉ ስምምነት መደረሱንም አስታውቋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶቹን ለማሳካት እንደ አመራር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል እንገባለን ነው ያለው፡፡

በክልሉ የሚስታዋለው ሌብነት፣ ጎጠኝነት፣ አመጽና የአድማ እንቀስቃሴዎች፣ ብልሹ አሠራር፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ጽንፈኝነትና አክራሪነት ክልሉን በእጅጉ እየጎዳና ኪሳራ እያስከተለ መሆኑን መገምገሙንም አስታውቋል፡፡ ችግሮችን ለሕዝብ በማስረዳት ለመፍታት ቃል መግባቱንም አመላክቷል፡፡ ሕዝብን በማስተባበር ክልሉን ከጽንፈኝነት አስተሳሰብ እና ከድርጊቶች አደጋ የጸዳ ለማድረግ ስምምነት ላይ እንደተደረሰበትም አስታውቋል፡፡

በውጭና በውስጥ የሚገኙ አፍራሽ ኃይሎች ሚዲያን በመጠቀም ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ለማተራመስ እንደሚሠሩ ያመላከተው መግለጫው ሕዝብና መሪዎችን የሚያቃቅሩ፣ አለመተማመን እንዲፈጠር የሚያደርጉ፣ በክልሉ መሪዎች ላይ ጥላችን የሚቀሰቅሱ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጿል፡፡ ክልሉን መሪ አልባ በማድረግ በጎችን የመቀራመት በተኩላዊ ቀመር የተሰላ የትግል ሥልት እየተገበሩ መሆናቸውንም አውስቷል፡፡ ይህም የመጣው ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ለሕዝባችን ከመስጠት አኳያ በተስተዋለብን ዳተኝነት ነው ብሏል፡፡

መሪዎች ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝባቸው ከማድረስ ባለፈ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራ ያለ አንዳች ማወላወል ለማስፈጸም መስማማታቸውንም አመላክቷል፡፡

የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የመልካም አሥተዳደር ጉድለት፣ ሌብነት እና ብልሹ አሠራር በሕዝብ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በኮንፈረንሱ መገምገሙን ያነሳው መግለጫው ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለማስወገድና የሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለማክሰም ቃል እንገባለን ብሏል፡፡

በኮንፈረንሱ የአመራር አስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ዝንፈት የሚታይበት፣ የጎራ መደበላለቅ እና የሚና ብዥታ የሚስተዋልበት፣ ከሕዝብ አገልጋይነት አንጻር የመንፈስ ዝለትና የሥነ ምግባር ብክለቶች ያለበት መሆኑ ያለ ሽንገላ ተፈትሿል ነው የተባለው፡፡ ከጽንፈኝነት የጸዳ፣ በሕዝብ አገልጋይነት ስሜት የሚዋጅ የአመራር ግንባታ ተግባራት ይፈጸማልም ተብሏል፡፡

የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች እንዲቀጥሉ፣ ችግሮችም እንዲፈቱ፣ የክልሉ ሕዝብ፣ መላው ኢትዮጵያውያን፣ ዲያስፖራዎች፣ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!