ባሕር ዳር: ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀምሯል፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ ክልሉ የተከፈተበትን ወረራ በመቀልበስ የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ እና የተጠናከረ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎችን መገንባት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ አሳይቷል ያሉት አፈ ጉባዔዋ በጦርነቱ ብዙ ዋጋ ቢከፈልም ሰላም መፈጠሩን የክልሉ ሕዝብ በአዎንታ አይቶታል ብለዋል፡፡ ለሰላም ስምምነቱ የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የነበረው ተሳትፎ ወሳኝ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን በግብርናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት አፈ ጉባዔዋ የበጋ መስኖ ስንዴ አበረታች አፈጻጸም በክረምቱም መደገሙን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡
በኮሮና ቫይረስ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃት እና የማዕድን ዘርፉን ማገዝ የተሻሉ ተግባራት ነበሩ ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊ አንድነቱ የማይደራደር እና ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ኾኖ ለዘመናት ሀገር ያጸና ነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ ይህንን ሕዝብ በተሳሳተ ትርክት ሌላ አተያይ እንዲሰጥ የተደረገበትን የተሳሳተ መንገድ ለማረም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ውሎው በተቋማት አፈጻጸም ይመክራል፤ ልዩ ልዩ ሹመቶችንም መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!