“የአማራን ሕዝብ ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው የተማረ ወጣት ማፍራት ሲቻል ነው” የአማራ ክልል ርእስ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር

0
120
“የአማራን ሕዝብ ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው የተማረ ወጣት ማፍራት ሲቻል ነው” የአማራ ክልል ርእስ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 10/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ዛሬ የመምህራንን ቀን አክብሯል፡፡ በዕለቱ በጡረታ ለተገለሉ መምህራን፣ በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ6 መቶ በላይ ውጤት ላስመዘገቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እና ለኮኮብ መምህራን እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በእውቅና ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእስ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን እውቅና እና ሽልማት መስጠቱ ምስጋና የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የመምህርነት ሥራ ትውልድን በእውቀት በመቅረጽ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጾ አለው፤ የሀገር ግንባታ ሥራን በአግባቡ ለመሥራት ደግሞ ትምህርት ወሳኝ ነው፤ ለትምህርቱ ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ የሚያበረክቱት ደግሞ መምህራን ናቸው፡፡
ሁሉም የመምህራን የልፋት ውጤት መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳድሩ መምህርነትን ማክበር የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ “የአማራን ሕዝብ ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው የተማረ ወጣት ማፍራት ሲቻል ነው” ብለዋል፡፡ ክልሉን ሊያግዙ የሚችሉ ልጆችን ለማፍራት የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
መምህርን በአግባቡ ያልያዘ መንግሥት ወደ ፊት መሻገር ስለማይችል ለመምህራን የሚከፈለውን ጥቅማጥቅም እንደሀገር ለማስከበር ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እየቀረበ መኾኑን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል፡፡
መምህርነት ተመርጦ የሚገባበት ሙያ እንዲሆን በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በርካታ የመምህራን ጥያቄዎችም መልስ ያገኛሉ ነው ያሉት ርእስ መስተዳደሩ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ለዓለም ጥላሁን እንዳስታወቁት ከ100 በላይ ጡረታ ለወጡ መምህራን፣ ለ29 ተማሪዎች እና ከ18 ጉድኝት ለተውጣጡ መምህራን እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል፡፡ ተሸላሚ ተማሪዎች በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ ኾነው በቀጣይም ጠንክረው በመማር ከራሳቸው አልፈው ለሀገር አቅም እንዲኾኑ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
እውቅና ከተሰጣቸው መምህራን መካከል መምህርት አሰፉ ረጋ የተደረገው እውቅና የበለጠ ለመሥራት የሚያበረታታ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ትምህርት የመምህራን ብቻ ባለመኾኑ መንግሥት መምህራን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በመመለስ፣ ወላጆች ልጆቻቸው ጠንክረው እንዲማሩ በመምከር እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሀገር አቀፍ ፈተና 650 ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ሳሙኤል መርሻ ባስተማሩት መምህራን ፊት መሸለሙ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡
በተለይም 2012 ዓ.ም ለመፈተን በእቅድ ተይዞ የነበረው የፈተና ጊዜ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መጓተቱ ጫና ሲፈጥርበት እንደቆየ ነግሮናል፡፡ ተማሪ ሳሙኤል ውጤቱም በትዕግስት እና ጠንክሮ በመሥራት የተገኘ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሳሙኤል ሁሉም ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለጥሩ ውጤት መሥራት ይገባቸዋል ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here