የአሚኮ ኅብር መጀመር መረጃ ከመስጠት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትርጉም እንዳለው ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

0
42

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አሚኮ ኅብር ሁለተኛ ቻናሉን ዛሬ አስጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ነብሩ ዝንጉርጉር በሚል የምንገለጽ ነን ብለዋል፡፡
ብዙ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና ሥነ ምኅዳር አለን ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ሁሉንም በአግባቡ ይዘን፣ እርስ በእርስ ተዋውቀን፣ ተከባብረን እና ተደማምጠን ከያዝናቸው የግጭት ምንጭ ሳይኾኑ የጌጥና የውበት ምንጭ ኾነው ያገለግላሉ ነው ያሉት፡፡
እርስ በእርሳችን ለመተዋወቅ ባለመዘጋጀታችን፣ ሚዛናዊና እውነተኛ መረጃ በየአካባቢው መድረስ ባለመቻሉ ልዩነቶችን እንደ ስጋት በመቁጠር በርካታ ግጭቶች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ በግጭቱ ተጠቂ የነበረው የአማራው ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም በሐሰት ትርክት ላይ ተጠምዶ፣ በጽንፈኝነት ጫፍ ተንጠላጥሎ ፣ ሕዝብን በጥላቻ መነጽር እያየ፣ አንዱን ከአንዱ እያጋጨ መኖር እንደ ልምድና እንደ ጀግንነት መቆጠር እንደተለመደም ጠቅሰዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት እናቁም ማለት በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ትውልድ እንፍጠር ማለት እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ ሀገረ መንግሥቱ ለሁሉም የሚያገለግልና ሁሉም የሚቀበለው ለማድረግ መቻቻልን፣ መከባበርን፣ መተዋወቅን በማስረጽ የበለጸገ ዜጋ እንዲፈጠር መረጃ መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ በአንድነት ሲቆም ለሰላም ጸር የኾኑ አካላት እየደከሙና አቅም እያጡ እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡ ለአብሮነት የመሠረት ድንጋይ ኾኖ የሚያገለግለው መቻቻል፣ መከባበርና መተዋወቅ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የተዛባ ትርክትንና ጥላቻን ማስወገድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ጥላቻንና የተዛባ ትርክትን ለማስወገደ መረጃ ወሳኝ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ መረጃዎች ትክክለኛና ሚዛናዊ ሊኾኑ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
መረጃዎች አብሮነትን፣ መከባበርንና መተዋወቅን መሠረት ያደረጉ መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ብዝኃ ልሳን ከማጠናከር አልፎ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲተዋወቁ የሚያደርግ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል በንግግራቸው ለመልካም ነገር ቅድሚያ በመስጠት ለሀገር ታማኝ ኾኖ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሚዲያ የሀገር አንድነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ነው ያነሱት፡፡
የአማራ ሕዝብ በጎረቤት ሀገራት ጨምሮ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ስም እንደሌለው ያነሱት ዶክተር ይልቃል ሚዲያው የተዛባውን ትርክት የማስረዳት ኀላፊነት እንዳለበትም አንስተዋል፡፡ ለሚጠሉንና ለሚወነጅሉን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ራስን ማስተዋወቅ አለብንም ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች እጣ ፋንታ በአንድነት የተጋመደ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ሚዲያው ያለውን ሃብት በፍትሐዊነት ተጠቅመን እንድንኖር መንገድ ይከፍታል ነው ያሉት፡፡
አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች፣ ሌላኛው ተጠቃሚ ሌላኛው ተጎጂ ኾኖ የሚቀጥልበት ሂደት እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡ ሁሉንም በፍትሐዊነት እና በእኩልነት መጠቀም አለብን ነው ያሉት፡፡ አሚኮ ኅብር የአብሮነትን ጥቅም የበለጠ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ በራሱ ብዝኃ ልሳን መኾኑን ያነሱት ዶክተር ይልቃል ሚዲያው ብዝኃ ልሳንን የሚያከብርና የሚያጎለብት እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡ ከሌሎች ወንድሞች ጋር እየተወያየንና እየተነጋገርን አንድነታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ያግዘናል ነው ያሉት፡፡
የአሚኮ ኅብር መጀመር መረጃ ከመስጠት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትርጉም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ አሚኮ ኅብር ተደራሽነቱን የሚያረጋግጥና ጥራት ያለው ቴክኖሎጂ ባለቤት መኾን እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ አሚኮ ኅብር ኅብር ኾኖ እንዲቀጥል የአማራ ክልል መንግሥት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን ለአሚኮ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ መደጋገፍ ሲኖር አብሮነትን የሚያጸና አብሮነትን የሚያስቀጥል ተቋም እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡
አሚኮ ኅብር እንዲመሠረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉት ርእሰ መስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/