ጎንደር፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የከተማ ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮችን ያካተተ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩ አቡሀይ ኮንፈረንሱ ስኬቶችን የምናስቀጥልበት ችግሮችን በሂደት የመንፈታበት መኾን አለበት ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ በበኩላቸው ውይይቱ ባሉ ችግሮች ተግባብቶ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማስቀመጥ መግባባት ላይ የሚደረስበት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
የአመራር አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይትን በማድረግ የክልሉ ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ከፍተኛ አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ነው ያሉት የብልፅግና ፖርቲ የጎንደር ከተማ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አወቀ አስፈሪ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችን እናሻግራለን ብለዋል፡፡
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የተጀመረው የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች ኮንፈረንስ ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲኾን የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች በመፍታት ላይ መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ከፍያለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!