አዲስ አበባ፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው ዓውደ ጥናት የተለያዩ የቴክኖሎጅ ሽግግርን የሚያሳዩ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለሀገራዊ ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለውና ከግብርናው ቀጥሎ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደኾነ ተናግረዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ቀጣይነት፣ ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት በማሳደግ ለሀገር ዕድገት የሚጫወተውን ሚና የላቀ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ የኾኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን ፣ አማራጭ ሀገር በቀል የግንባታ ግብዓቶችንና ቴክኖሎጅዎችን ማመንጨትና ማበረታታት፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉ አዳዲስ አዋጪና ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን ለሀገራችን ኢንዱስትሪ ማስተዋወቅ፣ ማላመድና ማስረጽ እጅግ አስፈላጊ መኾኑ አያጠራጥርም ብለዋል ኢንጅነር ወንድሙ፡፡
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ዘርፉን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እና ቴክኖሎጅዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጥናትና ምርምር በመለየት ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡና ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት ሙሉ እንዳሉት ኢንዱስትሪውን ከማዘመንና ተወዳዳሪ ከማድረግ አንጻር ሲጠኑና ሲዘጋጁ የቆዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ለኢንዱስትሪው ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማ እነዚህን የቴክኖሎጅ ሽግግር የፈጠራ ሥራዎች ለኢንዱስትሪው በማስተዋወቅ በኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲሰርጹና በሂደትም ጥቅም ላይ ውለው የኢንዱስትሪውን ችግር እንዲቀርፉ የሚስችል ግንዛቤን መፍጠር መኾኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!