“የታሪክ መዛግብት ሲፈተሹ ወልቃይት ማንነቱም ክብሩም አማራ ነው” መምህር ታየ ቦጋለ

0
326
ሁመራ: ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሸባሪው ወያኔ የተከዳበት ጥቅምት 24 በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ታስቧል፡፡
የሰማእታቱ ቀን በታሰበበት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ቃብትያ ተገኝተው ስለ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ሐሳባቸውን የሰጡት መምህር ታየ ቦጋለ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥቅምት 24ን አንረሳውም፣ ወልቃይትንም ብረሳሽ ቀኝ ትርሳኝ ያሉት መምህሩ በጋብቻ የተዛመደውን፣ ትምህርት ቤት የሠራውን፣ ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን ሠራዊት መካድ የማይረሳ ነው ብለዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊትን የካዱት ግፈኞች እና ጨካኞች መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊትን ሲክዱ ሕዝብ እና ኢትዮጵያን ወግተዋልም ነው ያሉት፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ደም ፈስሶ አልቀረም ብለዋል፡፡
የታሪክ መዛግብት ሲፈተሹ ወልቃይት ማንነቱም ክብሩም አማራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ለ30 ዓመታት የተጫነበትን በዓለም ታሪክ በመራራነቱ ሊመዘገብ የሚችልን መከራ አስወግዶ በመስዋእትነቱ ማንነቱን አስከብሯል ነው ያሉት፡፡
ወልቃይት ኢትዮጵያውያን ደም የከፈሉባት ናት ያሉት መምህሩ ወልቃይት በጠላት እጅ ተይዛ ቢኾን ኖሮ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን አሳልፈው ይሰጡን ነበርም ብለዋል፡፡ኢትዮጵያም አደጋ ውስጥ የምትወድቅበት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ወልቃይት ሳትደፈር የቆዬች፣ በትግል ጸንታ የኖረች ናትም ብለዋል፡፡
ከእውነት ፈላጊዎች እና ከተገፉት ጋር የሚቆሙት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ብለን አብረናችሁ እንቆማለንም ብለዋል መምህሩ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!