“የተፈጠሩ የታሪክ ስንጥቆች የሚሞሉት እውነተኛ ታሪኮችን በመሰነድ ነው” ረዳት ፕሮፌሰር ገንዘብ አታላይ

86

ደብረ ብርሃን: የካቲት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተገምደው ሀገርን አፅንተው ለዛሬ ትውልድ ሀገርን ከነ ክብሯ አስረክበዋል። ጠላት በመጣ ጊዜ የቤታቸውን ጉዳይ በመተው ጠላትን በእሳት ቀለበት ውስጥ በማስገባት አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው በመጣበት እግሩ እንዲመለስ አድርገዋል።
እልፍ ዘመናትን በነፃነት የኖረችው ኢትዮጵያ በብዙ ሺህ ቆራጥ ኢትዮጵያውያን መስዋእትነት ነው ይላሉ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ገንዘብ አታላይ።
“ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነት እሳቤ ያለፈ አፍሪካዊነትን ማዕከል ያደረገ ነፃነት እንዲመጣ የታገሉት የእነዛ ጀግኖች ልጆች ነን” ብለዋል የታሪክ ባለሙያው።
ከደቡብ ተነስቶ ሰሜን ኢትዮጵያ ድረስ ዘምቶ ለሀገሩ የተሰዋው፣ ከምሥራቅና ምዕራብ ተነስቶ በሀገሪቱ ጠረፎች ተሰማርቶ ድንበሩን የጠበቀው ከአድዋ እስከ ካራማራ ባሉ የድል ታሪኮች የተሳተፈው ሁሉ “ከሀገሬ በፊት እኔን ያስቀድመኝ” በማለቱ ነው ብለዋል።
ወንዝ አቋርጦ የመጣን ጠላት እንደ አመጣጡ በማስተናገድ ከእኛ አልፋ ለዓለም ተምሳሌት የሆነችን ሀገር መፍጠር የተቻለው በሀገር እና በእርስት ጉዳይ የሚደራደር ሀገረ መንግስትም ይሁን ሕዝብ ስላልነበረ መሆኑን የታሪክ ባለሙያው አስገንዝበዋል።
የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ሲጀመር በአርዓያነት የተነሳችው ኢትዮጵያ ነበረች የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በምሳሌነት ወስደው ለነፃነታቸው በር ከፍቶላቸዋል።
ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣን ጠላት አሳፍረን የላክነው አያቶቻችን ዛሬ እያሳየን ካለነው የብሔር ተኮር ንክሻ በፀዳ መንገድ ተጉዘው እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ከአድዋ ድል በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመበቀል ለዳግም ወረራ ስትመጣ ሺዎች በአደባባይ ደማቸው እንደ ጎርፍ ቢፈስም ሀገር ሀገር ናትና ለጠላት አሳልፈው አልሰጧትም ነው ያሉት።
በአሁኑ ሰዓት አላስፈላጊ የታሪክ ስንጥቃቶች ተፈጥረዋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ገንዘብ አታላይ እነኝህ የታሪክ ጉድፎች በዜጎች መካከል መቃቃርና መጠራጠርን ስለመፍጠራቸው አስረድተዋል።
በዚህም ያልተደረጉና ይደረጋሉ ተብለው ያልታሰቡ የጥፋት ድርጊቶች መፈጸማቸውን አብራርተዋል።
አሁን ላይ እያየን ያለነው ማንነት ተኮር ግድያ፣ የእርስ በእርስ መናቆር፣ መገዳደልና መበቃቀል እንዲሁም ብሔርን ቆጥሮ ማሳደድ የታሪክ ስንጥቃቱ መገለጫ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የተፈጠሩ የታሪክ መዛነፎችን ማስተካከል የሚቻለው ትክክለኛ ታሪካዊ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በማስረዳት መሆን እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል የታሪክ ባለሙያው።
ሙያን ለባለሙያ መተው ያስፈልጋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ገንዘብ አታላይ ችግሮችን ከማባባስ ወጥተን ትክክለኛ መረጃዎችን በማቅረብ እውነትን ይዞ ለመፍትሔው መታገል ለተሻለ ለውጥ ያበቃል ነው ያሉት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ መግባባትን ሊያመጡና የትላንትን የሀሰት ተረኮች ማስተካከል የሚቻለው ሁሉም ባለው አቅም ለእውነትና ለሀገር ጥቅም ሲሠራና ልክ እንደ አያቶቻችን በአንድነት ስንቆም ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:–ኤሊያስ ፈጠነ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/