ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በክልሉ ባደረሰው ዝርፊያና ውድመት፣ ለተጎዱ ወገኖች በሚደረግ አስቸኳይ ድጋፍ እና የደረሰውን ውድመት መልሶ በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በክልሉ በሰባት ዞኖች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ንጹኃንን በመግደልና ሀብት ንብረት በማውደም ግፍ መፈጸሙን በመግለጫቸው አንስተዋል። በቡድን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል በመፈጸምም ጭካኔ የተሞላበትን አረመኔያዊ ድርጊት አድርሷል ነው ያሉት።
በተወረሩት አካባቢዎችም በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ለረሃብ እና ለከፍተኛ ጉስቁልና ተዳርጓል ብለዋል አቶ ስዩም። አሸባሪው ቡድን በቁሳዊ ሀብት ላይ ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ እንደሆነም አስታውቀዋል። በደረሰበት ሁሉ ጤና ጣቢያዎችን እና ትምሕርት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ ማሕበራዊ ተቋማትን ከመዝረፍ ባለፈ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ አውድሟቸዋል ነው ያሉት። በውኃ ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመትም ሕዝቡ ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን አስታውቀዋል። የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል የተሠሩ የመስኖ ተቋማትን ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ ውድመት እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል።
አቶ ስዩም እንደገለጹት የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች እና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት አገልግሎት በማይሰጡበት ደረጃ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል። በኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶች ላይ ሰፋ ያለ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል። በኢንዱስትሪዎች ላይ ዝርፊያና ውድመት በማድረስም ከጥቅም ውጪ ማድረጉን ነው ያስታወቁት። በዚህም የኑሮ መሠረታቸው ያደረጉትን በርካታ ዜጎች ከሥራ ገበታ ውጪ አድርጓል። ለጉስቁልና ሕይወትም አጋልጧል ነው ያሉት።
ድልድዮችን አፍርሷል፣ መብራት፣ ስልክና የባንክ ተቋማት ዝርፊያ እና ውድመት ደርሶባቸዋል። በጥቅሉ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይም ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት። በሁሉም ዞኖች የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት በማይሰጡበት ደረጃ ወድመዋል።
በግለሰብ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ላይ ሳይቀር ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን አንስተዋል።
የአሸባሪው ቡድን የጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሀብቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በደን ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት በማድረስ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በእንስሳት እና በሰብል ልማት ላይ ያደረሰው ውድመትም ከፍተኛ ነው ብለዋል። የአርሶ አደሩን እንስሳት በመዝረፍ፣ አርዶ በመብላትና በጥይት በመግደል፣ ሰብል በማውደም አርሶ አደሮች ጥሪት አልባ እንዲሆኑ አድርጓል።
ይህ የሽብር ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ መረጃ የማበላሸት፣ የማጥፋት እና የማቃጠል ሥራ መሥራቱንም እንዲሁ ጠቅሰዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የሰው ልጅ ሊፈጽመው የማይገባ ውድመት በማድረስ በአማራ ላይ የጥላቻውን ጥግ አሳይቷል ብለዋል።
አካባቢዎቹ ነጻ ከወጡ በኋላ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተረባርቦ በፍጥነት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል። ከነበሩበት ከፍ ባለ ደረጃ ለማደራጀትም የስትሪሚንግ ኮሚቴ ተቋቁሟል። እንደ አቶ ስዩም ገለጻ የተቋቋመው ኮሚቴም እቅድ አዘጋጅቶ በኀላፊነት እየሠራ ነው የሚገኘው። የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማትና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተሳተፉበት የጥናት ቡድን የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማጥናት በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ተሰማርቷል ነው ያሉት። ጥናቱ ሲጠናቀቀም የውድመቱ መጠን ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚከናወኑ ተግባራትን አንስተዋል። የመንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ወደነበሩበት የመመለስ ተግባር፣ የጸጥታና የሕግ ማስከበር ተግባራት እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት የመመለስ ሥራ እየተከናወነ ነው። የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ሲሆን በቀጣይነትም መልሶ የማቋቋም ተግባሩ ይቀጥላል ብለዋል። የንጹህ መጠጥ ውኃ በተሽከርካሪ ማቅረብ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው። በዚህም ሕዝብ አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የተፈናቀሉትን የመመለስና የመቋቋም ሥራ በከፍተኛ ርብርብ እየተሠራ ነው። አሸባሪው ቡድን ወርሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ለሕዝቡ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለማድረስም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዜጎች ላይ የደረሰውን ግፍና የሀብት ውድመት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረደው ለማድረግም አካባቢዎቹን የማስጎብኘት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
መልሶ የመቋቋም ሥራው ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግ መሆኑን ያነሱት አቶ ስዩም የጉዳት ጥናቱ እንደተጠናቀቀ በስትራቴጂክ ፕላኑ መሠረት አካባቢዎቹ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ይደረጋል ነው ያሉት። ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ በመልሶ መቋቋም ሂደቱ የብዙ አካላትን ትብብር ይፈልጋል ብለዋል። ለዚህም የክልሉን ሕዝብና ባለሀብቶችና ኢትዮጵያዊያንና ዲያስፖራው ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
መልሶ ማቋቋሙ በቅንጅት፣ በትብብርና በመናበብ ይሠራል ያሉት አቶ ስዩም ተግባሩ በመንግሥት ደረጃ በተደራጀ አግባብ እንዲሠራ ይፈለጋል ነው ያሉት። አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ ሀብት ማሰባሰብ የጀመሩ አካላት መኖራቸውን በማንሳትም ይህ ተግባር እንዲቆም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/