“የተለያዩ የመሠረተ ልማት የሌለባቸው አካባቢዎች ቢገጥሙም ከኅብረተሰቡ ስለማይበልጡ ሳንታክት ልናገለግል ይገባል” የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የህክምና ዶክተሮች

0
28

“የተለያዩ የመሠረተ ልማት የሌለባቸው አካባቢዎች ቢገጥሙም ከኅብረተሰቡ ስለማይበልጡ ሳንታክት ልናገለግል ይገባል” የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የህክምና ዶክተሮች

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ጤና ሳይንስ ሲያስተምራቸው የቆዩትን 122 የህክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶክተር) የተለያዩ የጤና ችግር ያሉባቸው ዜጎችን በሀገር ውስጥ ሕክምና ለመስጠት በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ 10 የቅድመ ምረቃ፣ 23 የድኅረ ምረቃና 1 የማህፀን ካንሰር ሕክምና ፕሮግራሞች እንዳሉት ዶክተር ፍሬው አስረድተዋል።

ዩኒቨርስቲው በሕክምና ዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍና የህክምና አድማስን ለማስፋት በድንገተኛ አደጋዎችና ቃጠሎ፣ በጽኑ ህሙማን፣ በልብና ተዛማች ችግሮች፣ በኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ፣ በጉበትና ተያያዥ ህመሞች፣ የካንሰርና የማገገሚያ ሕክምና መስጫና ማስተማሪያ ማእከላትን ለማቋቋም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቦታ ለመስጠት ቃል መግባቱን ነው ዶክተር ፍሬው የተናገሩት።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶክተር) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ 861 የሕክምና ባለሙያዎችን ማፍራት ችሏል፣ በሕክምና ዘርፍ አገልግሎትም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

መንግሥት በርካታ የጤና ሕክምና ባለሙያዎችን እያስመረቀ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ተመራቂዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የጤና ሚኒስቴር ተገቢዉን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ከተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ዶክተር ይበልጣል ወርቅነህ እንደተናገሩት ለትምህርት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ስኬታማ ያደርጋል። ውጤታማ ለመሆን ከሁሉም በፊት ወኔና ዓላማ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል። “ቃል በገባሁት መሠረት ኅብረተሰቡን በእኩልነት ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ” ብለዋል።

በከፍተኛ ማዕረግ ከተመረቁት ውስጥ ዶክተር ማኅደር ማዘንጊያ ከልጅነቴ ጀምሬ ለፈተና ሳይሆን ለዕውቀት አነብ ነበር፤ ሁሉም ሰው ለማወቅ ቢያነብ የሚፈልገውን መፈፀም እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡ የዛሬ ምሩቃን ጊዜና ቦታን ሳንመርጥ ኅብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅበናል፤ የተለያዩ የመሠረተ ልማት የሌለባቸው አካባቢዎች ቢገጥሙም ከኅብረተሰቡ ስለማይበልጡ ሳንታክት ልናገለግል ይገባል” ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here