
ገንዳ ውኃ፡ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራብ ጎንደር ዞን አጠቃላይ ካለው የደን ሽፋን 30 በመቶው በእጣን ዛፍ የተሸፈነ ነው።
ይሕ ሃብት ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ እንደሚገኝ ነው በመተማ ወረዳ ለምለም ተራራ ቀበሌ በእጣንና ሙጫ ማምረት የተደራጁ ወጣቶች ለአሚኮ የተናገሩት።
በእጣንና ሙጫ ማምረት ላይ ያገኘናቸው የኑስ ዲቦ እንዳሉት ከሃብቱ የሚገኘው ገቢ ከሰሊጥ፣ ጥጥና ማሽላ ምርት ከሚገኘው ገቢ በአስር እጥፍ ብልጫ አለው። በ2014 ዓ.ም 1 ኩንታል እስከ 23 ሺህ ብር ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ነው ለአብነት ያነሱት።
በዚህም የአብዛኛው የማኅበሩን አባላት ሕይወት መለወጡን ነው የገለጹት።
ሌሎች ያነጋገርናቸው የማኅበሩ አባላትም የእጣን ዛፍ ያለውን ኢኮኖያዊ ጠቀሜታ በመረዳት ከሰደድ እሳትና ከደን ጭፍጨፋ ጥበቃ እያደረጉ መኾናቸውን ነግረውናል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትና የአካባቢ ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ሀብታሙ አድጎ፤ ምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው 760 ሺህ ሄክታር መሬት የሚጠጋ የደን ሽፋን ውስጥ ከ230 ሺህ በላይ የሚኾነው በእጣን ዛፍ የተሸፈነ መኾኑን ገልጸዋል።
ታዲያ ይህ ሃብት ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሚጠበቀው ልክ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ነው ያነሱት።







አቶ ሀብታሙ እንዳሉት የእጣን ዛፍ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ አምራቾች በዘመናዊ ማምረቻ መሳሪያ እንዲያመርቱ ተደርጓል፤ ባለሙያዎችም የአመራረት ሂደቱን ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፤ የሕገ ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ ሰደድ እሳት እና ሌሎች ችግሮችን ለመከላከል የጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል፤ በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥበቃ እየተጠናከረ መምጣቱንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!