የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመሥገን ጥሩነህ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ለዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

95
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

አዲስ አበባ: መስከረም 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመሥገን ጥሩነህ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸው አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ መቻቻል፣ መከባበርና መፈቃቀድ የሰፈነበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲረጋገጥም ሁሉም ተባብሮ እና ተደማምጦ የሚሠራበት እንዲሆንም አሳስበዋል።
‹‹መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የስኬትእንዲሆን በራሴ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ስም መግለጽ እወዳለሁ›› ያሉት አቶ ተመሥገን፤ በተለይ የኢትዮጵያን ኅልውና ለማረጋገጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግዳጅ ላይ የምትገኙ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እና የጥምር ጦሩ አባላት መላው ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ የሕይወት ዋጋ ጭምር እየከፈላችሁ በመሆኑ ክብር ይገባችኋል ነው ያሉት፡፡
‹‹ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አዲሱ ዓመት ለሰላም በምትከፍሉት መስዋእትነት በአዳዲስ የድል ብሥራቶች የሚታጀብ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት እገልጻለሁ፡፡ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ›› ያሉት አቶ ተመሥገን፤ የተቋሙ አባላትም የሥጋት ቀጣና በሆኑ አውደውጊያዎች ጭምር በመሠማራት መረጃ በመሰብሰብ፣ በመተንተንና ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውል በማድረግ ሀገራዊ ግዳጃቸውን እየተወጡ በመሆኑ አክብሮቴና የአዲሱ ዘመን መልካም ምኞቴ በያሉበት ይድረሳቸው ብለዋል፡፡
በመልዕክታቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ሰላምን አበክራ ትሻለች፡፡ የሰላሙ መንገድ ዛሬም ክፍት ነው፡፡ ይህን ባለመቀበል ጦርነትን የቀሰቀሱ አካላት ዛሬም የሰላምን ዋጋ ተረድተው በአዲስ ዓመት በአዲስ መንገድ እንዲጓዙ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ያሉት አቶ ተመሥገን፤ በሀገር ኅልውና የተቃጣውን ጥቃት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የጥምር ጦሩ በብቃት መመከታቸውን ወደፊትም ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም በተጠናቀቀው ዓመት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎች በመታጠቁና የላቀ ብቃት ያለው የሰው ኃይል አቅም በመገንባቱ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በአሸናፊነትና በጽናት እንድትሻገር ብርቱ ጉልበት ሆኗል፤ በእርግጥም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለዋል፡፡
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J