ባሕር ዳር:መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲው የስድስት ወር አፈፃፀም ላይ ባካሄዱት ውይይት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎችን በአግባቡ መከወን የሚያስችል መዋቅር ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል።
አመራሮቹ በፓርቲው የስድስት ወራት አፈፃፀም ላይ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት አጠናቅቀዋል።
በመድረኩ ላይ በርካታ ሐሳቦች ተነሥተው ምክክር የተደረገባቸው ሲሆን የፓርቲውን የውስጠ ዴሞክራሲ ባሕል በማሳደግ በቀጣይ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ትግል በማድረግ የታዩ ጥንካሬዎችን ይበልጥ በማስፋት እንዲሁም ድክመቶችን አርሞ በመሄድ ረገድ ሰፊ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎችን በአግባቡ መከወን የሚያስችል መዋቅር በማጠናከር ከዋና ጽህፈት ቤት እስከ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ድረስ የተሰናሰለ የተግባር አፈፃፀም እንዲኖር ለማስቻል ከፍተኛ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
የብልፅግና ፓርቲን መርሆች፣ ስትራቴጂዎች እና ፖሊሲዎችን ወደ ኅብረተሰቡ ዘንድ በተቀናጀ መልኩ በማስረፅ በመደመር እሳቤ የተዋጀ የብልፅግና መንገድ መፍጠር ትልቁ የቤት ሥራ እንደሆነ በመገንዘብ ቀጣይ የርብርብ ማዕከል መሆን እንደሚገባውም መግባባት ላይ መደረሱን ከፓርቲው ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!