የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲው የ6 ወራት አፈጻጸም ላይ እየተወያዩ ነው።

258
ባሕርዳር: መጋቢት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲው የስድስት ወራት አፈጻጸም ላይ እየተወያዩ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፥ ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛ ጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና በምርጫ ለሕዝቡ የገባውን ቃል በውጤታማነት ለመፈፀም በከፍተኛ ትጋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአመለካከትና በተግባር የተዋሃደ አመራር በማረጋገጥ ቅቡልነት ያለው ፓርቲ በመገንባት የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና እርካታን ማረጋገጥን ዋና አላማው አድርጎ ወደ ስራ እንደገባም አንስተዋል፡፡
ይህን መሰረት አድርጎ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በስድስት ወራት ውስጥ የተሰሩ ስራዎች ይገመገማሉም ነው ያሉት።
May be an image of 1 person and standing
በውይይቱ የፓርቲው የዋና ጽህፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ዘርፍ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ መገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየትና በቀጣይ አፈፃፀሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥራ ለመስራት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል።
በውይይቱ ከስድስት ወራት አፈፃፀም ግምገማ በተጨማሪ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የሱፐርቪዥን ቡድን በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውሮ ያገኛቸው ግኝቶች ላይ ሰፊ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!