የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ ለመቀልበስና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን አረጋገጠ።

0
62

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አሽባሪው የሕወሃት ቡድን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀረበውን የሠላም አመራጭ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል።

በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

አሸባሪው ህወሃት ባለፉት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የብዝሃ ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ባለቤት የሆነችውን የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ እና ብሔር ብሔረሰቦችን እርስ በርስ ለማፋጀት ሌት ከቀን ሲሠራ ቆይቷል። በዚህ ክፉ ሴራው በርካታ ንጹሃንን ህይወት በመቅጠፍ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቁር ጠባሳ ፈጽሟል።
ይህ አሸባሪ ቡድን በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታ በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈጠረው ጥርጣሬ፣ መከፋፈልና እልቂት ሳያንሰው የጥፋት ሴራ ሁነኛ ዋነኛ መገለጫው ማድረጉን ደጋግሞ አሳይቷል። በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት ጀምሮ የትግራይ ወጣቶችን ወደ ጦርነት በማስገባት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ግልጽ ጦርነትና ወረራ ያደረሰው እልቂት አሸባሪ ቡድኑ ለሰብዓዊነት ምንም የማይራራ አረመኔ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

አሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎቹን በመጠቀም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካቢዎች ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል። በርካታ ውድመትንም ፈጽሟል።

የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት እንቅልፍ የሚነሳው ይህ አሸባሪ ቡድን ተላላኪዎቹን ተጠቅሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ከወንድም የኦሮሚያና የአማራ ክልል ሕዝቦች ጋር ለመነጠል በክልሉ ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጋር የሚዋሰኑ የመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች እንዲሁም የማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ አካባቢዎችን የጦርነት ቀጠና የማድረግ ክፉ ሴራውን ሲፈጽም ቆይቷል።

አስቸጋሪ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ የሚችሉት ኢትዮጵያዊያን ግን የዚህ አሸባሪ ቡድን ባንዳነት የበለጠ አጠነከራቸው እንጂ በጋራ እንዳይቆሙ አልገደባቸውም። ለህዝብ ሠላም ኃላፊነት የሚሠማው የኢትዮጵያ መንግስት ግልጽ የሠላም አማራጭን ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ተጨባጭ ሂደት ገብቷል።

ነገር ግን ያለፈው ጥፋት አልበቃው ያለው አሸባሪው ህወሃት ወትሮም ቢሆን ከጦርነትና እልቂት ውጪ መኖር እንደማይችል ያሳየበትን ተግባሩን አሁንም በድጋሚ ቀጥሎበታል። አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን የሠላም ጥሪ በእምቢታ ረግጦ የትግራይን ወጣት ለጥፋት በመጠቀም በአማራና አፋር ክልሎች ዳግም ጦርነት ማወጅን ምርጫው አድርጓል።

መፍትሔው በሠላም ተወያይቶ መፍታት ሆኖ እያለ አሸባሪው ህወሃት አሁን የጀመረው ዳግም ጦርነት ለሕዝብ ሠላም ከመጨነቅ ይልቅ የብዝሃነት ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ መቼም የማይተኛ መሆኑን ደጋግሞ ያረጋገጠበት መሆኑን ያሳያል።

አሁንም ቢሆን አሽባሪው የሕወሃት ቡድን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀረበውን የሠላም አመራጭ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል።

ዓለማቀፉ ማኅበረሰብም በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ዳግም ወረራ ከማውገዝ በተጨማሪ ለህዝቦች ሠላም ሲባል በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሠላም አማራጭ አሸባሪ ቡድኑ እንዲቀበል አስፈላጊውን ትብብርና ግፊት የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን ጨምሮ ህዝባዊ ማዕበልን በመጠቀም በአማራና አፋር ክልሎች አያካሄደ ያለውን ወረራ በጽኑ ያወግዛል።

የክልሉ መንግስት አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ ለመቀልበስና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት እንደከዚህ ቀደሙ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሌም ዝገጁ መሆኑን ያረጋግጣል።

አሸባሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ አየቀረበለት ያለውን የሠላም አማራጭ በድጋሚ በማጤን የማይቀበል ከሆነ እና ወረራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ለህዝብ ደኅነነት እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ሲባል በፌዴራል መንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚደግፍ እና ኃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ለማረጋገጥ ይወዳል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም
አሶሳ