የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ከ43 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበትን ባለ ስድስት ወለል የእንግዳ ማረፊያ ሕንጻ ገንብቶ አስመረቀ።

237

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ከ43 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወጭ የተደረገበትን ባለ ስድስት ወለል የእንግዳ ማረፊያ ሕንጻ ገንብቶ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ሕንጻውን ገንብቶ ያጠናቀቀውን የባሕርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ አመስግነዋል።

ለምዕመናኑ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ብፁዕ አቡነ አብርሃም እግዚአብሔር የሰው ልጆች ይህችን ምድር እንዲያሳምሯት፣ እንዲያስውቧት፣ በላባቸው፣ በድካማቸው ወጥተው ወርደው እንዲጠቀሙባት ፈጥሯል ብለዋል።

ብጹዕነታቸው መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 36 ቁጥር 11 ላይ “ቢሰሙ ቢያገለግሉትም ዕድሜያቸውን በልማት፤ ዘመናቸውን በተድላ ይፈጽማሉ” ብሏል ብለዋል። የሰው ልጅ በሥራው ደስ እንዲሰኝ እግዚአብሔር ፈቅዶለታል። እግዚያብሔርን ያገለገለ ሰው ዕድሜውን ለጥላቻ፣ ለጸብ ፣ ለውዝግብ፣ ለንትርክ እና ለማፍረስ ሳይኾን ለልማት ይጠቀምበታል ብለዋል። የተራቡ የሚበሉበት ፣ የተቸገሩ የሚጠለሉበት የታረዙ የሚለብሱበትን፣ ሥራ ያጡ ሥራ የሚያገኙበትን እና ራሳቸውን የሚረዱበትን ልማት እንዲያለሙ እግዚአብሔር ፈቅዶላቸዋል ብለዋል።

በጎ የሚሠሩ ዘመናቸው ሁሉ የተድላ ነው። ጸጸት የሌለበትን ሕይወት ይመራሉም ብለዋል። ብጹዕ አቡነ አብርሃም ስብሐተ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ቀዳሾች እና አወዳሾች የዕለት እንጀራ ማግኘት የሚችሉት ሠርተው ጥረው ግረው ካገኙት መኾን አለበት ብለዋል።

ይህንንም ዛሬ የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ ሕንጻ ጊዮርጊስን ገንብቶ አሳይቶናል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ አብርሃም ሕንጻ ጊዮርጊስ እንዲገነባ እና ለዚህ እንዲደርስ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ያበረከቱትን መላከ ገነት አባ ሐይለማርያምን ማስታወስ ተገቢ ነው ብለዋል።

ሕንጻ ጊዮርጊስ እንግዳ ማረፊያ ከእንግዳ ማረፊያ በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሠጡ ክፍሎች አሉት ብለዋል። እንግዳ ተቀባይነት የኢትዮጵያውያን ብሎም ለባሕር ዳር ልዩ መገለጫ በመኾኑ እንግዳ ተቀባይነታችንን በዘመናዊ መንገድ ለማድረግ የወሰድነው እርምጃ ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል።

የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አስተዳዳሪ መላከ ገነት ቆሞስ አባ ወልደትንሳዔ ባንቲገኝ በበኩላቸው ሀጢያት ከጸናባት ቦታ ከማደር የእግዚያብሔር ጥበቃ ባለበት ቦታ ማደር የተመረጠ ነው ብለዋል። ይህን ሕንጻ ገንብተን ለማጠናቀቅ በርካታ ውጣ ውረድ የታየበት ቢኾንም ዛሬ ያሠብነው ተሳክቶ ለዚህ ለመብቃቱ የተራዱንን በሙሉ እናመሰግናለን ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ አስራት ሙጬ የእንግዳ ማረፊያው የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማገዝ በኩል ድርሻው ከፍተኛ ነው። ሕንጻ ጊዮርጊስ የማረፊያ ቤት እጦትን ከመቅረፉ በተጨማሪ ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ አገልግሎቶች እያደረገችው ያለውን ተሳትፎ የሚያሳይ እና ለሌሎችም አስተማሪ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!