የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የሂዩማን ብሪጅ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

0
62
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የሂዩማን ብሪጅ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ድጋፉ ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ወደፊ ለሚገነቡት የህክምና ተቋማት የሚውል ነው ተብሏል።
የድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር የሽጌታ ገላው (ፕሮፌሰር) የድጋፍ የህክምና ቁሳቁስ በቀጣይ የሚገነቡት የጤና ተቋማት በሥራ ላይ ሲውሉ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ታካሚዎችን ሊያስቀር ይችላል ብለዋል።
በአማራ ክልል ያሉ ሆስፒታሎች የሚሰጡት አገልግሎት ከሕዝቡ ብዛት አንፃር በቂ እንዳልኾኑ የጠቆሙት ፕሮፌሰር የሺጌታ ኮሌጁ ባዘጋጀው የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚችል የሕክምና ተቋማት ለመገንባት በሥራ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ለሚገነቡት የሕክምና ተቋማት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የግንባታ ቦታን ለመስጠት ቃል እንደገባላቸውም አስረድተዋል።
የሚገነቡት ተቋማት ለካንሰር ህክምና፣ ለኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ ለልብ ህመም ህክምናና ለሌሎች ህክምናዎችም እንደሚያገለግሉ አስረድተዋል። “እነዚህ ተቋማት ተገንብተው ሥራ ሲጀምሩ ባሕር ዳር የህክምና የቱሪዝም ማዕከል ትኾናለች” ነው ያሉት። ከሂዩማን ብሪጅ ጋር በድጋፍ የተፈራረሙት የህክምና ቁሳቁስም ዕቅዳቸውን ለማሳካት ትልቅ ግብዓት እንደሚኾን ተናግረዋል።
የድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት የሂዩማን ብሪጅ የአፍሪካ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዳሙ አንለይ (ዶክተር) ድርጅታቸው ከአሁን በፊትም የአማራ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ለህክምና አገልግሎት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾን በርካታ የህክምና ቁሳቁስን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን ጠቁመዋል። “በአማራ ክልል ከአሁን በፊት ድርጅቱ ለሁሉም ሆስፒታሎች ድጋፍ አድርጓል” ያሉት ኀላፊው ድጋፉ ለታለመለት ዓላማ እስከዋለ ድረስ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ለህክምና ከሚውል ቁሳቁስ በተጨማሪ ድርጅቱ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማስረከብ በማጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር አዳሙ ገልጸዋል።
ዛሬ የተደረው ድጋፍ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ለአልትራሳውንድ፣ ለቀዶ ጥገና፣ ለተመላላሽ ሕሙማን፣ ለጨረራና ሌሎች ለከፍተኛ ህክምና የሚውሉ ቁሳቁስ ናቸው።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here