የባሕር ዳር ከነማ እና የስሑል ሽረ አሰልጣኞች ምን አሉ?

0
162

“በህመምና በቀይ ካርድ ምክንያት አራት ተጫዋቾቻችን አለመምጣታቸው በእጅጉ ጎድቶናል።” የስሑል ሽረ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ

”ተጋጣሚያችን በጠንካራ የመከላከል ስልትና ቶሎ ቶሎ በመልሶ ማጥቃት እንደሚጫወት አውቀን ነው ወደ ሜዳ የገባን።” የባሕር ዳር ከነማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባሕር ዳር ከነማ እና ስሑል ሽረ ተጫውተዋል። በጨዋታውም ባሕር ዳር ከነማ 1ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኞቹ ለአብመድ አስተያዬት ሰጥተዋል። የስሑል ሽረ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ “ነጥባችን ተቀራራቢ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነበር፤ ተጋጣሚው ቡድን የቆመ ኳስ እንዳይጠቀም ስጋት ነበረን” ብለዋል።

በቆመ ኳስ ግብ እንደተቆጠረባቸውም ተናግረዋል። በህመምና በቀይ ካርድ ምክንያት አራት ተጫዋቾቻቸው ወደ ባሕር ዳር አለመምጣታቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸውም ነው አሰልጣኙ የተናገሩት።

የባሕር ዳር ከነማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ተጋጣሚው ቡድን በጠንካራ የመከላከል ስልትና ቶሎ ቶሎ በመልሶ ማጥቃት እንደሚጫወት አውቀው እንደገቡ ተናግረዋል። ባሕር ዳር ከነማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ዝቅተኛ ግብ አስቆጥሮ ከማሸነፉ ጋር ተያይዞ “አንድ ለዜሮ ከሚያሸንፍ ቡድን ሶስት ለሁለት የሚረታ ቡድን ቢኖረኝ ደስ ይለኛል” ብለዋል፡፡

ምክንያታቸው ደግሞ ተመልካቹ በግብ ስለሚደሰትና ሰለሚዝናና ነው፡፡ የባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ቡድን የመከላከል ችግር እንዳለበት ያነሱት አሰልጣኙ በትናንቱ ጨዋታ ግብ አለመቆጠሩ በተከላካዮቹ ላይ የስነ ልቦና እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ መርሃ ግብር ከሜዳ ውጭ ነጥብ በማግኘት ቡድኑ መሻሻል እንዳለበትም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ