የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

0
125

የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚውል የ10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

ገንዘቡ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በኩል በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ እንደሚውል ፋውንዴሽኑ አስታውቋል።

የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ድጋፍ ሀገራቱ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የፋኦ ዋና ዳሬክተር ኪው ዶንግዩ ልገሳውን አመሥግነው ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም መሰል ድጋፍ በማድረግ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮችን ኑሮ ለመቋቋም እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አንድ ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የበረሃ አንበጣ መንጋ በአንድ ቀን 35 ሺህ ሰዎችን መመገብ የሚችል ሰብል እንደሚያወድም ድርጅቱ ገልጿል።

የበረሃ አንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከ25 ዓመታት፣ በኬንያ ደግሞ ከ70 ዓመታት በኋላ በአስከፊ ሁኔታ የተከሰተ ነው ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በቀጣናው ለሚታየው የምግብ እጥረት በዚህ ዓመት ይዞ የነበረውን 76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት ወደ 138 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ማድረጉንም አስታውቋል።

ምንጭ፡- የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት

በየማነብርሃን ጌታቸው

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here