ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በድምቀት በሚያከብሩ የተለያዩ የዓለም ሀገራት ለወዳጅ ዘመድ ስጦታ የመስጠት ሰፊ ልምድ አለ። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ሀገራት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ” የስጦታ በዓል” ተብሎ ይጠራል። ይኽ ወቅትም ከሌላው ጊዜ በተለዬ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ የሚነቃቃበት ነው። በሀገራችንም ይህንን በዓል ጠብቆ ስጦታ የሚሰጥና የሚቀበል የማኅበረሰብ ክፍል ቁጥሩ ቀላል የሚባል አይደለም።
አቶ ቢኒያም ጌትነት በባሕርዳር ከተማ ከሚገኙ የግል ባንኮች በአንዱ ተቀጥረው የሚሠሩ የሒሳብ ባለሙያ ሲኾኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲደርስ ለባለቤታቸው ስጦታ የመስጠት ልምድ እንዳላቸው ነግረውናል። “ባለቤቴ በየዓመቱ ለልደት በዓል ስጦታ ካልሰጠኋት ቅር ይላታል” የሚሉት አቶ ቢኒያም እሳቸውም ቢኾን ባለቤታቸው ስጦታ ካልሰጠቻቸው በዓሉ የተሟላ እንደማይመስላቸው እና ይህንንም ከእጮኝነት ጊዜያቸው እስከ ትዳር ሕይወታቸው በደስታ እየፈፀሙት ያለ የፍቅር መግለጫ እንደኾነ ይናገራሉ። አቶ ቢኒያም አንዳንድ ጊዜ የመዋቢያ ዕቃዎች አንዳንዴም ጌጣጌጥን በስጦታነት ለባለቤታቸው ያበረክታሉ።
“የስጦታ በቅሎ ጥርሱ አይታይም” በማለት የሚገልጹት አቶ ቢኒያም ማንኛውም ሰው ለሚወደው ሰው አስቦ ከሚያዘጋጀው ስጦታ በላይ ትልቁ ቁምነገር ለስጦታ ተቀባዩ ያለው ፍቅር እና ክብር ነው ይላሉ። ስጦታ ተቀባዩም ቢኾን ከተሰጠው የቁስ ስጦታ ይልቅ የስጦታው አዘጋጅ ይህን ስጦታ ለመስጠት በአእምሮው ያሰበውን ሀሳብ ነው ስጦታ አድርጎ ሊቀበል የሚገባው ብለዋል። ስጦታ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስተኛ ያደርጋልና ስጦታ መስጠት የሚችል ሁሉ በመስጠት ደስታውን ማጣጣም ይችላል ሲሉ ሀሳባቸውን ያስረዳሉ።
በስጦታ ዕቃዎች ንግድ ላይ የተሰማራው ወጣት አንለይ ቢራራ በበኩሉ በባሕርዳር ከተማ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መቃረብን ተከትሎ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ የስጦታ ዕቃዎች ሸማች እንደሚበዛ ይገልጻል። በአብዛኛው በዓሉ ከመድረሱ አንድ ሳምንት አስቀድሞ በቁጥር በዛ ያሉ ወጣቶች የስጦታ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚመጡ ሲኾን ብዙዎቹ ለተቃራኒ ፃታ ጓደኞቻቸው ስጦታ ሲገዙ ይታያል። ከስጦታ ካርድ እስከ እጅ ሰዓት እና ሽቱዎች ድረስ በብዛት ይሸመታሉ የሚለው ወጣት አንለይ የገና በዓል የስጦታ ዕቃዎች ገበያ የሚደራበት ወቅት እንደኾነም ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀዲስ ኪዳን መጽሐፍት መምህር የኾኑት እና በተለያዩ የአደባባይ ንግግሮቻቸው የሚታወቁት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንደሚሉት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን እና ስጦታ የመሰጣጣት ልማድን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ስጦታ ባሕላዊ ትውፊት ብቻ ሳይኾን ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ እና መመሪያም ነው” ብለዋል።
መጋቤ ሐዲስ እሸቱ “በመጀመሪያ የስጦታ መነሻ የኾነው የመጀመሪያው ሰጪ እግዚአብሔር ነው። አዝርዕቱን፣ አየሩን፣ ውኃውን፣ አፈሩን፣ ንፋሱን፣ ጨረቃውን፣ ከዋክብትን በጠቅላላ የምናየውን ሁሉ ፈጥሮ፣ በነፃ የሰጠን እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ስጦታ ሰጥቶ የልቡ ስላልደረሰ ደግሞ መጨረሻ ላይ ክርስቶስ ራሱን ሰጠን” ስንል እናምናለን ብለዋል።
“ስጦታ ሁለት አይነት ነው” የሚሉት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ይህንን ሲያብራሩም መልሶ የሚጠበቅ ስጦታ እና መልሶ የማይጠበቅ ስጦታ ይሏቸዋል፡፡ ለጓደኛ የሚደረግ ስጦታ በተዘዋዋሪ ብድር ማለት ነው፡፡ መልሶ ጓደኛችን ሌላ ስጦታ ይሰጠናል፡፡ በሌላ በኩል መልስ የማይፈልገው ደግሞ ለድሆች፣ ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ ለተራቆቱ የሚደረግ ነው ብለዋል።
ሰብአ ሰገል እጣን፣ ከርቤ፣ ወርቅ … ለኢየሱስ ክርስቶስ እጅ መንሻ ይዘው መጥተዋል፡፡ ይኸውም ለስጦታ እንደመነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል በማለት ያብራራሉ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ተከትሎ በአብዛኛው የበዓሉ አክባሪ ዘንድ የሚከናወነውን አሁን ላይ ያለውን ስጦታ የመሰጣጣት ልምድ ሲገልጹም ሰብአ ሰገል ለክርስቶስ ያቀረቡትን ስጦታ እንደ መነሻ ብንወስድም ረቂቁ የምዕራባውያን ተፅዕኖ አለበት ብለዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የገና ዛፍ ገበያ የሚደራበት፣ ፖስት ካርድ የሚሸጥበት፣ ከክርስቶስ ልደት ይልቅ አሻንጉሊት የሚከበርበት የፈንጠዚያ በዓል ኾኗል የሚሉት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ሙሽራው ተረስቶ ሚዜዎቹ የሚታጀቡበት በዓል ኾኗል ብለዋል፡፡ ይሄ የምዕራባውያን ባሕል ወረራ ውጤት ነው ሲሉም ስጦታው ለድኾች ከመመጽዎት ጋር እንዲገናኝ ቢደረግ ሲሉ መክረዋል፡፡ ስጦታ የሃይማኖት መመሪያ እንደኾነ በማሳሰብ በዛው ልክ ሊከናወን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በፍራኦል ወርቅነህ (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል በተግባር በልምምድ ላይ ያለ ተማሪ)
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!