የበረሃ አንበጣ መንጋው ከየአገራቱ የሚመጣ ስለሆነ አንድ አገር ወይም አህጉር ብቻውን የሚከላከለው ስላልሆነ አገራት በጋራ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

0
125

ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2013ዓ.ም (አብመድ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በተለያዩ ወረዳዎች ተከስቶ የነበረ የበረሃ አንበጣ መንጋ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የግብርና መምሪያ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና ማኅበረሰቡ በጋራ ባደረጉት ርብርብ ከባቲ ወረዳ በስተቀር ሊመክቱት እንደቻሉ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳደር እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ኢብሬ ከበደ ተናግረዋል፡፡ በባቲ ወረዳ ግን በ14 ቀበሌዎች ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ መሆኑን አቶ ኢብሬ አስረድተዋል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋው ከተከሰተ ጀምሮ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ1 ሺህ 250 ሄክታር ሰብል ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው በአመዛኙ ጉዳቱ በባቲ ወረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “አርሶ አደሩ፣ ባለሙያው እና ኃላፊዎች በጋራ ርብርብ ባያደርጉ ኖሮ በብሐየረሰብ አስተዳደሩ ምንም ዓይነት ሰብል አይገኝም ነበር“ ያሉት አቶ ኢብሬ መንጋው ያልደረሱ ሰብሎች በስለው እስኪነሱ ድረስ ሊቆይ እንደሚችልም ስጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

መንጋው የሚንቀሳቀሰው ፀሐይ ቀን በመሆኑ ሰብል ላይ የሚያድር ከሆነ ሰብሉን ሊያወድም ስለሚችል በተቻለ መጠን ቁጥቋጦ ላይ እንዲያድር ትግል ሲደረግ እንደቆየም የመምሪያ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋው ከአካባቢው እስኪወገድ ድረስ መላው የብሔረሰብ አስተዳደሩ ማኅበረሰብ የተለመደ ርብርቡን ሊቀጥል እንደሚገባም አቶ ኢብሬ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ መንጋ የተከሰተው በበርካታ አገራት ነው፡፡ በተለይ በህንድ፣ የመን፣ ሰሜናዊ ሶማሊያ ሰፊ የበረሃ አንበጣ መንጋ ስለነበረ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት ቀደም ሲል መንጋው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ይህንን የኢፌዴሪ ግብርና ሚንስትር ድኤታ ወንዳለ ሀብታሙም አረጋግጠዋል፡፡

አሁን በምሥራቅ አማራ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ የክልል እና የፌድራል የሥራ ኃላፊዎች በቦታው በመገኘት ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ሚንስትር ድኤታው ተናግረዋል፡፡ “በተለይ መንጋው በሠፊው በሚገኝበት በአፋር ክልል መርጫ አውሮፕላኖች፣ መርጫ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች፣ የሚያስተባብሩ እና ለልየታ የሚያገለግሉ የሞተር ሳይክሎች፣ ኬሚካሎች እና የመርጫ መሣሪያዎች እንዲሁም አስፈላጊ የሆነውን የሰው ሀብት በስፍራው በማድረስ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልልም የተቻለውን ያክል ድጋፍ እያደረገ ነው“ ያሉት አቶ ወንዳለ ከመንጋው ሥፋት እና አደገኛነት አንፃር የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥታት ተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

“የበረሃ አንበጣ መንጋው የተከሰተው በአፋር ክልል ብቻ ቢሆን አዚያው በእንጪጩ ማጥፋት ይቻል ነበር“ ያሉት ሚንስትር ድኤታው መንጋው ከየአገራቱ የሚመጣ ስለሆነ አንድ አገር ወይም አህጉር ብቻውን የሚከላከለው ሳይሆን አገራት በጋራ ርብርብ ሊያደርጉት የሚገባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ መንጋው ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊቆይ እንደሚችልና የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋው ዑደቱን ጠብቆ ሊቆይ እንደሚችልም አቶ ወንዳለ አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here