የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድንን በመደምሰስ ወርቃማ ድል እየተጎናጸፉ መሆኑን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የመቅደላ ብርጌድ አባላት ገለጹ፡፡

0
332
መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጋሸና ግንባር የሚገኙ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በጠላት ላይ የላቀ የበላይነት እያገኙ እንደሆነ አባላቱና መሪዎቹ ተናግረዋል።
ሳጅን ካሳዬ ወርቁ በጋይንት ግንባር ያለው የአማራ ልዩ ኃይል ተጋድሎ አኩሪ እንደነበረ ተናግሯል። ልዩ ኃይሉ ከጋሳይ ጀምሮ እስከ ደብረ ዘቢጥ ጀብድ ፈጽሟል ብሏል። የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይሉ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድንን በተቀናጀ መልኩ እንደደመሰሱት ገልጿል።
ጠላት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ለማስረከብ እንደተገደደም አስረድቷል። ኮንስታብል አሳልፍ ተመሰለው ልዩ ኃይሉ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድንን እንደደመሰሱት ተናግሯል። የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን ነፃ እስኪሆኑ ድረስ ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነው የተናገረው።
ኮንስታብል እህቱ ጌታ በጠላት ላይ የተቀዳጁት ድል ወርቃማ እንደነበር ገልጻል “እኛ መቼም ቢሆን ወደ ኋላ አንመለስም፤ ጠላትን ከወንዶች እኩል እየታገልኩና እያሸነፍኩ ነው፤ ጠላት ቀድሞ ቢመሽግም ምሽጉን መስበር ችለናል፤ ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት ጠላት ሬሳውን እንኳን ማንሳት አልቻለም” ብላለች። ለሕዝቡ ነፃነት ሲባል ዝናብ፣ ብርድና ፀሐይን ችለው እንደሚታገሉም አስረድታለች።
ረዳት ኢንስፔክተር አስፋው አረጋ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ብዙ ጀግኖችን ያፈራ ለቀናት መዋጋት የሚችል ትኩስ ኃይል ነው ብለዋል። አባላቱ የጠላትን ምሽግ በማፍረስም ይታወቃሉ ነው ያሉት። “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሲተኩስ ልክ እንደ አባቶቹ ከአንገት በላይ መምታት እንዳለበት አምኖ ነው ጠላትን የሚቀጣው” ብለዋል።
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድንን ከአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ከየትም ቦታ ሙሉ በሙሉ ለማጽዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ወንድሞቹ ጋር በመናበብ፣ እጅና ጓንት ሆነው ጠላትን በመደምሰስ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል። ለትግላቸው ስኬት የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ደጀንነት ወሳኝ መሆኑንም ረዳት ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የመቅደላ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል አዱኛ አለማየሁ በመቄት ወረዳ ፍላቂት አካባቢ ጠላት የመጨረሻውን እድል የወሰነበት ነው ብለዋል። ጠላት የተጠቀመበት አካባቢ ለውጊያ አስቸጋሪ ቢሆንም የተለያየ የውትድርና ስልቶችን በመጠቀም ሳይመለስ እንዲቀበር አድርገነዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለአንድ ዓላማ ነው የሚታገሉት ያሉት አዛዡ በቅርቡ ጠላትን ቀብረን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድልን እናበስራለን ብለዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን ከደቡብ ጎንደር ዞን ጋሳይ ከተማ ጀምሮ እስከ ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ድረስ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ሊማር በሚችልበት ሁኔታ እንደተቀጣ ተመልክቷል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ