የሽብርተኛው ትህነግን ፍፃሜ ለማፋጠን የፀጥታ ኀይሉ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እየተወጡ መሆኑን የመቄት ወረዳ ሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ተናገሩ፡፡

0
167
ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ወረራ በርካቶች “ዱር ቤቴ” ብለው እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡ በመንግሥት እና በግል የታጠቁት እና እምቢ ለወራሪ ያሉት የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት በገቡበት ጫካ ውስጥም ኾነው የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በመከታተል እና ፊት ለፊት በመፋለም አኩሪ ገድል ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ይገኛሉ። አኩሪ ጀብዱ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሰሜን ወሎዋ መቄት አንዷ ነች፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት በገቡበት እና በደረሱበት ቦታ ኹሉ አስነዋሪ እና አሰቃቂ ወንጀሎችን ቢፈጽሙም ከአካባቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሽንፈት እንዲለቁ የወጣቱ፣ የሚሊሻ አባላት እና የሕዝቡ ተሳትፎ አኩሪ ነበር፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በአካባቢያችን ዘልቆ በመግባት ተራ ስርቆት እና ዝርፊያ ፈጽሟል ያሉን የሕዝባዊ ሠራዊት አባል አለልኝ ወንድምነው የደረሰው ውድመት አስከፊ ቢሆንም ጠላት በፀጥታ ኀይሉ ክፉኛ ተመትቶ አካባቢውን ከለቀቀ አንድ ወር አልፎታል ብለውናል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ በአካባቢው ቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ሙሉ በሙሉ ግብዓተ መሬቱ እስኪፈጸምም በጥበቃ እና በተለያዩ ወታደራዊ ድጋፎች የተጣለባቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
በግዳጅ ቀጣናዎች የፀጥታ ኀይሉ የሚሰጠንን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣን ነው ያሉን ደግሞ የሕዝባዊ ሠራዊቱ አባል ፈንቴ መንግሥቴ ናቸው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር በመቀናጀት ከግዳጅ እስከ ደጀንነት በቅንጅት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኮማንድ ፖስት እና የወረዳው የሥራ ኅላፊዎች የቅርብ ድጋፍ እና ክትትል እንዳልተለያቸውም ገልጸዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በአካባቢያችን ዘልቆ እንደገባ የፈጸመውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል ያሉን ሌላው አስተያየት ሰጭ የሕዝባዊ ሠራዊት አባል ንጋት አዱኛው የሽብር ቡድኑን አባላት ከገቡበት ገብቶ ማሳደድ አማራጭ አልባ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ወጣቱ፣ ሕዝቡ እና ሕዝባዊ ሠራዊቱ በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች እና የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት በግዳጅ ቀጣና በመሰለፍ ሊያግዙ ይገባል ያሉት የሕዝባዊ ሠራዊት አባሉ ወቅቱ የአማራ ሕዝብ በተባበረ ክንድ ጠላትን የሚያስወግድበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከሌሎች አጎራባች አካባቢዎች እና በወረዳው ውስጥ የተደራጁ የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት የሽብር ቡድኑን ፍፃሜ ለማፋጠን ከወገን ከፀጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፈው እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በላይ ኅብረት እና ቅንጅት በማሳየት ግፍ እየተፈጸመባቸው ያሉትን አካባቢዎች ነፃ ማውጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሕዝባዊ ሠራዊት አባላቱ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ በተለይም አማራ ረፍት እንደማይኖረው ጠቁመው ለጋራ ነፃነት በጋራ መቆም ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከመቄት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ