የስፔን ላሊጋ ወደ ውድድር ተመልሷል፤ ሊዮኔል ሜሲም ግብ ማስቆጠር ጀምሯል፡፡

0
493

በኮፓ ኢጣልያ ደግሞ አቻ የተለያዬው ናፖሊ ለፍጻሜ ደርሷል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የኮሮናቫይረስ ሥርጭት በቁጥጥር ሥር ባይውልም የእግር ኳስ ውድድሮች መካሄድ እየጀመሩ ነው፡፡ የስፔን ላሊጋም ከሰሞኑ ወደ ውድድር ተመልሷል፡፡

የሊጉ መሪ ባርሴሎና ወደ ማሎርካ ሜዳ አቅንቶ በ4 ለ0 ድል ተመልሷል፤ ሊዮኔል ሜሲ በባከኑ የጭማሪ ደቂቃዎች 4ኛውን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ቀሪዎቹ የባርሴሎና ግቦች በቪዳል፣ ብሬትዌት እና አልባ የተቆጠሩ ናቸው፡፡

በላሊጋው የ28ኛ ሳምንት ሌሎች ጨዋታዎች እስፓኞል አላቬስን 2ለ0፣ በሜዳው አሸንፏል፤ ከሜዳቸው ውጭ ደግሞ ሪያል ቫላዶሊድ ሌጋኔስን 2ለ1 እና ቪላሪያል ሴልታቪጎን 1ለ0 አሸንፈዋል፡፡

ላሊጋውን ባርሴሎና በ61 ነጥብ እየመራ ነው፤ ሪያል ማድሪድ በ56 ነጥብ ይከተላል፤ በእርግጥ ማድሪድ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታውን ገና አላካሄደም፡፡ እስፓኞልና ሌጋኔስ በእኩል 23 ነጥብ እንዲሁም ማሎርካ በ25 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ፡፡

በጣልያንም የኮፓ ኢጣሊያ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ትናንት ምሽት ተካሂዷል፤ ናፖሊ ኢንተርሚላንን ያስተናደበት የምሽቱ ጨዋታ በአንድ አቻ ተጠናቅቋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም አንድ ለባዶ አሸንፎ የነበረው ናፖሊ በድምር ውጤት 2ለ1 ለፍጻሜ ደርሷል፡፡

በምሽቱ ጨዋታ ክርስቲያን ኤሪክሰን በ2ኛው ደቂቃ ከማዕዘን መትቶ በቀጥታ ባስቆጠራት ግብ የናፖሊ ማሸነፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ ነገር ግን ቤልጀማዊው አጥቂ ድሬስ መርቲንስ በ41ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳውን ለፍጻሜ አድርሷል፡፡

ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ኮፓ ኢጣሊያን ያሸነፈው ናፖሊ የምሽቱን ጨዋታ በአቻ ቢያጠናቅቅም ለፍጻሜ አልፏል፡፡ የግቧ ባለቤት መርቲንስ ለናፖሊ 122 ግቦችን በማስቆጠርም አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡