“የሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጉብኝት ወቅታዊውን የኢትዮ-አሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያለዝበው ይችላል” ረዳት ፕሮፌሰር በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር)

0
46
“የሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጉብኝት ወቅታዊውን የኢትዮ-አሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያለዝበው ይችላል” ረዳት ፕሮፌሰር በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር)
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሉን ባስታወቀ ማግስት ድርጊቱን አጥብቀው ተቃውመዋል፤ በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ እና የኦክላሃማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ፡፡ ሰውየው ሀገራቸው የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ይጎዳል ያሉትን እና የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የሚያሻክረውን የጉዞ እገዳ ከመጣል ይልቅ ኢትዮጵያውያንን ከጎናቸው ሆኖ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ሽንጣቸውን ገትረው ሞግተዋል፡፡
ሴናተሩ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካን ውስብስብ ፖለቲካ እና የአሸባሪው ትህነግን ረጅም የሴራ እጆች በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ አሜሪካ በቀጣናው የምታራምደው የጂኦ ፖለቲካል ግንኙነት ከመስመር ስቶ አግላይ እና ደጋፊ እንዳይሆን ሚዛን ጠባቂ አስተያየቶችን በብቸኝነት ሰንዝረዋል፡፡ ሀገራቸው “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ፖሊሲዋን እርግፍ አድርጋ ትታ እና የሁኔታዎችን ወቅታዊ አሰላለፍ ተረድታ ድጋፍ እና ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድታራምድም ወትውተዋል፡፡
ሴናተር ጂም ኢንሆፍ በሀገራቸው ሳሉ ከሚያሳዩት የኢትዮጵያ አጋርነት ሌላ ከሰሞኑ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ሴናተሩ በግላቸው ይምጡ ለሥራ ጉዳይ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በተለይም ከአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር በነበራቸው ቆይታ በህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት፣ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት፣ በሱዳን ድንበር ውዝግብ እና ሌሎች ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል ተብሏል፡፡ ይህም ሴናተሩ ከግላቸው ይልቅ መንግሥታዊ ተልዕኮ ይዘው እንደመጡ ፍንጭ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ከሴናተሩ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር ተያይዞም የሁለቱን ሀገራት የሻከረ ግንኙነት ለመቀየርና ለኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ምን እገዛ ይኖረው ይሆን? የሚሉ ሀሳቦች ይነሳሉ፡፡ ይህን በተመለከተም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር) የሚሉት አሉ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መርህ ምንጊዜም ቢሆን ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም ይገባል ባይ ናቸው የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ፡፡ ይህም አሜሪካ ከአንድ ሀገር ጋር የሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመሰላት እና ብሔራዊ ጥቅሜን ያስጠብቃል ብላ ባሰበች ጊዜ በበጎም በክፉም ልትቃኘው ትችላለች ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ከሰሞኑ የተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ምንጩ ብዙ ቢሆንም የህዳሴው ግድብ ኹለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት፣ ሕግ የማስከበር ርምጃ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በባዕዳን ላለመጠምዘዝ የሚያደርገው ጥረት ድምር ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር በዕውቀት እነዚህ የልዩነት ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ ክፍተቶቹን በቀላሉ ሊሞላ የሚችል የዲፕሎማሲ ጥረት ብልጫ አለመውሰድ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ተከታትሎ በማምከን በኩል የተፈጠረ ውስንነት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ሴናተሩ ኢትዮጵያን በሚገባ ከማወቃቸው ጋር ተያይዞ የችግሩን ምንጭ ስለሚረዱ የባይደን አስተዳደር የጣለውን የጉዞ እገዳ ማዕቀብ መቃወማቸውን ዶክተር በዕውቀቱ ገልጸዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ጋር መወያየታቸው ደግሞ ነባራዊ ሁኔታውን በሚገባ ለመረዳት ያግዛቸዋል ነው ያሉት፡፡ እናም የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ መንግሥት እንደ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ሌሎችን መሳብ እና እውነታውን ማሳየት ይገባዋል፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን በእውቀት እና በጥበብ መምራት ይጠበቅበታል፤ በግለሰቦች እና በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን በመዋቅራዊ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here