የሱማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የመጀመሪያ ክልላዊ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።

0
43
የሱማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የመጀመሪያ ክልላዊ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሱማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የማሳደግ ዓላማ ያለው የመጀመሪያው ክልላዊ የዳያስፖራ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የዳያስፖራ አባላት አሏት።
በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የዲያስፖራ ብዛት ያላት ስትሆን፤ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ አባላት በትውልድ ሀገራቸው ላይ ያላቸው ተሳተፎ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
“የዳያስፖራ አባላት የሬሚታንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አቅማቸውን ሀገራቸው ላይ ማዋል ጀምረዋል፤ የክህሎት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ሚናቸው የጎላ ሆኗል” ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራቸው ማስገባት እንደቻሉም ጠቁመዋል።
በ3 ሺህ 186 አዳዲስ የሂሳብ ቁጥሮች ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ መቆጠብ ተችሏል ብለዋል።
“ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰብ ችለዋል፤ 847 የዳያስፖራ አባላትም የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ተደርጓል” ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራ አባላትን ተሳትፎና ንቅናቄ በዘላቂነት ለማሳደግ ከጎናቸው ሆኖ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አብዱላሂ በበኩላቸው “አብዛኛው ሰው ስደት ሲባል ቀድሞ የሚያስታውሰው አሉታዊ ተጽዕኖውን ብቻ ነው” ብለዋል።
“ይሁን እንጂ በየትኛውም ዓለም ያሉ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጉልህ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አላቸው” ሲሉ ጠቅሰዋል።
የዳያስፖራ አባላት በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አጋር ሆነው እየሠሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በዚህም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ብቻ በዓለም ላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የሄዱ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በሦስት እጥፍ ማደጉን ጠቁመዋል።
ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 2019 የዳያስፖራ አባላት ሬሚታንስ ወደ 550 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
“ይሄም የተቀባይ ሀገራትን የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም የልማት አጋዥነት ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው” ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ የክልሉን 30 በመቶ አጠቃላይ ምርት እንደሚሸፍንና ለሀገሪቷ እድገትም የማይናቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና በሱማሌ ክልል ኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ሥራ የጀመረው የሱማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ ፕሮግራም የአባላቱን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here