“የሰው ልጅ ነፃነትን ፈላጊ ነው፤ ነፃነት ግን በነፃ አይገኝም” የሕልውና ዘማቾች

0
230

ጥቅምት 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአሸባሪው ትህነግ ከተወጋች ዓመት ሊሞላት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ “መብረቃዊ” ያሉትን ክህደት ፈፀሙ፡፡ ላለፉት 12 ወራትም ከሕግ ማስከበር ዘመቻ እስከ ሕልውና ዘመቻ ኢትዮጵያ ተገድዳ በገባችበት ጦርነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም የአሸባሪው ትህነግ ወረራ ለመቀልበስ በትግል ውስጥ ናቸው፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ የተጣባት ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ተወግታ ብዙ ጊዜ ደምታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከካራ ማራ እስከ ኢትዮ-ኤርትራ ካሳለፈችው ጦርነት ጀርባ ሽብርተኛው ትህነግ ረጅም እና ህቡዕ የሴራ እጆች ነበሩበት፡፡ የህልውና ዘመቻው ግን ምንም እንኳን ምዕራባውያን አጋፋሪዎች እና የጎረቤት አጨብጫቢዎች ቢኖሩበትም ሽብርተኛው ትህነግ ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ ጠላትነቱን በግልጽ ያሳየበት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር በብሔር፤ ሃይማኖት በሃይማኖት ላይ እንዲነሳ ሲደረግ ሽብርተኛው ትህነግ ራሱ ሸምጋይ እሱው ገላጋይ፤ ራሱ ሕግ አስከባሪ እሱው መካሪ ሆኖ እርስ በርስ ሲያባላ ቆይቷል፡፡

ዛሬም ሽብርተኛው ትህነግ “መቃብሩ ሲማስ እና ልጡ ሲራስ” እንኳን የሸራረበው ሴራ በየቦታው ሲተረተር እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ ባለ ማግስት ካለፉት ወራት ጀምሮ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ወረራ ፈጽሟል፡፡ በወረራው ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች የተፈጠሩበት የአማራ ክልልም የክተት ዘመቻ ጥሪ ከሁለት ወራት በፊት አውጆ ነበር፡፡ አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ወረራ ሕዝባዊ ማድረጉን ተከትሎ ሕዝባዊ ማዕበል መፍጠር ብቸኛው አማራጭ ነው ያለው የአማራ ክልል መንግሥት ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻውን በሚችለው ሁሉ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቦ እየተሠራ ነው፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ እባብየ እና መምህር ፀዳሉ ፈንታውም የክተት ዘመቻውን ተቀብለው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉ ዘማቾች ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ወራትም ከጉና እስከ ጋሸና የወገን ጦርን ተቀላቅለው ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

“የሕልውና ዘመቻ” ማለት የሀገር የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ማለት ነው ያለን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በሕልውና ዘመቻው የአንድ ክፍለ ጦር የዘመቻ ክፍል አባሉ ሲሳይ እባብየ ነው፡፡ መምህር ሲሳይ ይህ ዘመቻ የኢትዮጵያ መቀጠል አለመቀጠል እና የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የመኖር ያለመኖርን የሚወስን ጉዳይ ነው ብሏል፡፡

በተከፈተብን ሕዝባዊ ወረራ ልክ ሕዝባዊ ማዕበል አልፈጠርንም የሚለው ሲሳይ “የሰው ልጅ ነፃነትን ፈላጊ ነው፤ ነፃነት ግን በነፃ አይገኝም” ነው ያለን፡፡ መምህር ሲሳይ ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻውን ሊደግፍ እንደሚገባም ምክረ ሐሳቡን ያስቀምጣል፡፡ የመጀመሪያው ዘመቻውን በመቀላቀል እስከ ሕይዎት መስዋእትነት ከፍሎ ትውልድን እና ሀገርን መታደግ፡፡ ያልቻሉ ለወገን ጦር ትጥቅ እና ስንቅ የሚሆን የሎጀስቲክስ እና የግንዛቤ ፈጠራ መሥራት ነው፡፡

ሌላው ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህሩ ፀዳሉ ፈንታው የክልሉን መንግሥት የክተት ጥሪ ተቀብሎ ትግሉን እንደተቀላቀለ ነግሮናል፡፡ ከደብረ ታቦር ጀምሮ የወገን ጦር ከጠላት ጋር ባደረገው ፍልሚያ እንደተሳተፈ የነገረን መምህር ፀዳሉ እናት ስትደፈር፣ ሀገር ስትወረር እና ወገን ሲንገላታ ቁጭ ብሎ መመልከት ተገቢ አይደለም ብሎናል፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ የተወሰኑ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ የሕልውና ስጋት መሆኑን የገለጸው መምህር ፀዳሉ አማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች በመሆናቸው ግንባር ቀደም ተጎጂዎች መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

መምህሩ “አሁን የምንችለውን አለማድረጋችን ምናልባትም ነገ የማንችለውን እንድንሸከም ልንገደድ እንችላለን” ብሏል፡፡ እናም ወጣቱ የሕልውና ትግሉን በመቀላቀል ሀገርን ከብተና ወገንን ከሰቆቃ መታደግ ይኖርበታል ሲል መክሯል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከመቄት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m