የሰሜን ጎንደር ዞን የአማራ ፋኖ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ህልውና ዘመቻው መቀላቀሉ ተገለጸ፡፡

0
585

የሰሜን ጎንደር ዞን የአማራ ፋኖ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ህልውና ዘመቻው መቀላቀሉ ተገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን የአማራ ፋኖ ለህልውና ዘመቻ ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት አጠናቆ ለዘመቻው ስምሪት መውሰዱን የሰሜን ጎንደር ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የሰው ሀብት አደረጃጀት እና የጸጥታ ስምሪት ቡድን መሪ ሰለሞን አለባቸው እንደተናገሩት ከዞን በተለያዩ አደረጃጀቶች የታቀፈው የጸጥታ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይልና ከተለያዩ ክልሎች ከተወጣጡ ልዩ ኀይሎች ጋር ጁንታውን እንዲደመስስ ስምሪት መሠጠቱን ተናግረዋል።

የአማራ ፋኖ አደረጃጀትም ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት አጠናቆ ስምሪት ተሠጥቷል፤ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ ከመከላከያ ሠራዊትና ከልዩ ኀይል ጋር በመኾን አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመቅበር ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ወደ ዘመቻ ገብቷል ብለዋል።

ስምሪት ከተሠጣቸው የአማራ ፋኖ መካካል ፋኖ መሉነህ ማስረሻ እንደገለፁት አሸባሪውን ቡድን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ከፍተኛ ዝግጅት አድርገናል።
“የምንታገለው የአማራን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ነው” ያሉት ፋኖ ሙሉነህ ኅብረተሰቡ ለአሉባልታ ጀሮ ባለመስጠት በሚችለው ልክ ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ከዚህ በፊት በተደረገው ጦርነት የፋኖን ጀብድን ጠንቅቆ ያውቃል፤ አሁንም ለጥፋት የተዘጋጀውን ቡድን ከመንግሥት የጸጥታ ኀይል ጋር በመሆን እስከ መጨረሻው እንሸኘዋለን ነው ያሉት።

የአማራ ፋኖ የአሸባሪውን ቡድን ሕገ ወጥ ሥራ ከባለፋት ዓመታት ጀምሮ በተጠናከረ አካሄድ እየተፋለመ መምጣቱን የነገሩን ደግሞ ሌላኛው ስምሪት የተሠጣቸው ፋኖ አንተነህ ድረስ ናቸው።

አሸባሪው ቡድን ፊት ለፊት የመዋጋት አቅምና ዝግጁነት እንደሌለው የገለጹት ፋኖ አንተነህ ድባቅ እየተመታ መሆኑን ሕዝቡ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።

ፋኖ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ የሀገር ነቀርሳ የኾነውን አሸባሪ ቡድን ለመቅበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፋኖ መብራቱ አረጋ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ ከዚህ በፊት ወልቃይት እና ሁመራ በኀይል ሲይዝ ላለማስደፈር ትግል ማድረጋቸውን አስረድተዋል። የውሸት ፋብሪካ የሆነው አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሚያሠራጨው የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ መሸበር አያስፈልግም ነው ያሉት።

ፋኖ መብራቱ የአሸባሪውን የትህነግ ሴራ በመገንዘብ የዕድሜያቸውን ግማሽ ያክል ቡድኑን እየታገሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው – ከደባርቅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here