ባሕር ዳር:መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ “በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የቆየው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን የንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ላለፉት ወራት በተከናወኑ የማኅብረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ሥራዎች ሴቶችን ከተጠቂነት መከላከል መቻሉን ገልጸዋል።
ሀገራችን ላለፋት ጊዜያት ያጋጠማት ሰው ሰራሸ ችግሮችን ለመታደግ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባሕላችንን ለማስቀጠል የምንሰራበት ጊዜ ነውም ብለዋል።
የተለያዩ የፓናል ውይይቶችን በማካሄድና በሰላም ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ፣ በየደረጃው ያሉ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በሴቶች ጉዳይ ሲሰራ መቆየቱንም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል፡፡
በአፋር ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላሰተር አስተባባሪ አሚና ሴኮ በበኩላቸው ፥ የሰላም እሴቶችን ለመገንባት የሴቶች ሚና የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የሠላም ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንደአን ጨምሮ ከተለያዩ የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!