“የራዲዮ ተደራሽነት ውስን መሆን ለተዛባ የመረጃ ስርጭት መበራከት ድርሻ አለው” ጀማል ሙሃመድ (ዶክተር)

0
134
“የራዲዮ ተደራሽነት ውስን መሆን ለተዛባ የመረጃ ስርጭት መበራከት ድርሻ አለው” ጀማል ሙሃመድ (ዶክተር)
ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዛሬ የዓለም የራዲዮ ቀን ነው፡፡ እንደ ዛሬው ምድራችን በረቀቁ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ከመጥለቅለቋ በፊት፣ ነገሮችን በአንድ ትንሽ የስልክ ቀፎ ማከናወን ከመቻላችን በፊት ያኔ አንድ እንደ ብርቅ የሚታይ ውድ እቃ ነበር- ራዲዮ፡፡
ዘነበ ወላ “ልጅነት” በተሰኘው ልብወለድ መጽሐፉ በውብ ቋንቋ እንዳስቃኘን በዛን ዘመን ራዲዮ ምንም እንኳን ተደራሽነቱ እና የነበራቸው ሰዎች ጥቂቶች ቢሆኑም በማኅበረሰቡ ዘንድ የጎላ ተጽዕኖ ነበረው፡፡ በቀን ውስጥ ለውስን ሰዓታት የሚያስተላልፋቸው መረጃዎች እና ፕሮግራሞች በጉጉት የሚጠበቁ እና አይረሴ ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ ተጽዕኖው ቀላል የማይባለው ራዲዮ በየዓመቱ ይታወሳል፡፡
የዓለም ራዲዮ ቀንን ከማክበር በስተጀርባ ያለው ዋናው ቁም ነገር የሬዲዮን አስፈላጊነት ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ማሳወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ራዲዮ መረጃን ለአድማጭ ለማድረስ ውጤታማ መንገድ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አባል ሀገራት 2011 (እ.አ.አ) የራዲዮ ቀን እንዲከበር በሃሳብ ደረጃ ቀረበ፡፡ በ2012 (እ.አ.አ) በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የካቲት 6 ቀን (ፌብሪዋሪ 13) በየዓመቱ የራዲዮ ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወሰነ፡፡
የዓለምን የድህነት እና የጭቆና ቀንበር ከገፈፉ የብዙኃን መገናኛ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል- ራዲዮ፡፡ አጠቃቀሙ ቀላል፣ በቀላሉ ተደራሽ እና ምስል ከሳችነቱ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅም አድርጎት ዘልቋል፡፡
ራዲዮ በዓለም ደረጃ የበርካቶችን አመለካከት የቀየረ፣ እይታን የዘወረ እና የጋራ መግባባትን ያሰፈነ የመገናኛ ዘርፍ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ “በድህነት ዓለም ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ሕዝቦች የራዲዮ ውለታ እጅግ ከፍተኛ ነው” ያሉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ጀማል ሙሃመድ (ዶክተር) ናቸው፡፡
ዛሬ ለዘመነው የዓለማችን የመገናኛ አውታሮች ዓይነት እና መጠን መበራከት ራዲዮ እርሾ ሆኗል ብለዋል፡፡ የራድዮ ስርጭት አገልግሎት አጀማመር በኢትዮጵያ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተለያየ የጊዜ መነሻዎችን ቢያመላክቱም መዝሙር ሐዋዝ “የብዙኃን መገናኛ እድገት በኢትዮጵያ” መጽሐፉ እንዳስረዳው የራዲዮ ስርጭት አገልግሎት ጣቢያ ለማቋቋም 1923 ዓ.ም በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ አካባቢ መሰረተ ድንጋይ ተጣለ፡፡ ከዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ መስከረም 2/1928 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ንግግር ሥርጭት ጀመረ፡፡ የሬድዮ ጣቢያው የመጀመሪያው አንባቢ ወይም ጋዜጠኛ፣ ታላቁ ጸሐፊ እና የክብር ዶክትሬት ባለቤቱ ከበደ ሚካኤል ነበሩ፡፡
ግብርና የምጣኔ ሃብቷ የጀርባ አጥንት፣ አርሶ አደሩ የሀገሪቱ ዋልታ ሆኖ ለዘመናት በዘለቀባት ኢትዮጵያ የራዲዮ ጥቅምና ግልጋሎት ቀላል እንዳይደለም ነው ዶክተር ጀማል ያስረዱት፡፡
በከተማ እና በገጠር መካከል ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት እየተፈጠረ መጥቷል የሚሉት ምሁሩ መንግሥት በዓመት ውስጥ ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ራዲዮን ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ ሊሠራ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
“የራዲዮ ተደራሽነት ውስን መሆን ለተዛባ የመረጃ ስርጭት መበራከት ድርሻ አለው” ብለዋል ዶክተር ጀማል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ አርሶአደሮችን ማዕከል ያደረገ የመገናኛ ብዙኃን በተለይም የራዲዮ ተደራሽነትን ማስፋት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- ከድረ ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ