የምግብና ሥነ ምግብ ጤና ስትራቴጂና ፖሊሲን የሚያሳካ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው፡፡

0
28

የምግብና ሥነ ምግብ ጤና ስትራቴጂና ፖሊሲን የሚያሳካ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምግብና ሥነ ምግብ ጤና ስትራቴጂና ፖሊሲን ለማሳካት የሚያስችል ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ትግበራ መግባቱን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ጥናቱ በቅርቡ የፀደቀውን የቀጣይ 10 ዓመታት የምግብና ሥነ-ምግብ ጤና ፖሊሲና ስትራቴጂን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ጥናቱን በዋናነት የሚፈፅሙ፣ የሚያስፈፅሙና የሚመሩ ከ500 በላይ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና የቤተ ሙከራ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የተግባር ልምምድ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጥናቱ የእናቶችና የህፃናት ጤናን ጨምሮ የሥነ ምግብ ችግሮችን ከመሰረቱ ለማስወገድ የሚያግዝ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ጥናቱ ከ16 ሺህ በላይ አባወራዎችና ከ30ሺህ በላይ ግለሰቦችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ለጥናቱ ማስፈጸሚያ 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

በጥናቱ ለሚሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ አጠናቃሪዎችና ተንታኝ ባለሙያዎች በቂ ሎጂስቲክስ መመደቡን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣት ሴቶች፣ እናቶችና መላው ማኅበረሰብ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ማገዝ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በየዕለቱ የሚሰበሰበውን መረጃ በቀጥታ ወደ ማእከል የዳታ ቋት ለማስገባት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሥነ ምግብ ምርምር ዳይሬክተርና የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ዶክተር ማስረሻ ተሰማ በበኩላቸው ጥናቱ በሁሉም ክልሎች ሥር የሚገኙ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮችን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የምግብና ሥነ ምግብ ሥርዓትን ከመሰረቱ ለመቀየር የሚያስችል ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቅ የመጀመሪያ ሀገራዊ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል።

ከእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ከሥነ ምግብ ሥርዓት ጋር ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ 16 በመቶ የሚሆነውን አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
“በዚህም በሀገሪቱ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የመቀንጨር ችግር፣ የቫይታሚን፣ የአይረንና የዚንክ እጥረትና ሌሎች ጤናና ጤና ነክ ችግሮች አለባቸው” ብለዋል።

ሁሉንም የእድሜ ክልሎች የሚያማክለው ይህ ጥናት በቅርቡ የፀደቀውን የምግብና ስነ ምግብ ፖሊሲና ስትራቴጂን ለማስፈፀም የወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ለውጤታማነቱ ትክክለኛ ግብዓት ለማግኘት ጭምር የሚካሄድ መሆኑን አመላክተዋል። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here