የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ርምጃ እንዲጠናከር እንደሚሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

305
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ርምጃ እንዲጠናከር እንደሚሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መንግስት እየወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ርምጃ ብዥታዎችን የማጥራት ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች፤ በኢኮኖሚ፣ በዜጋ ዲፕሎማሲና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳዮች ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ዓበይት የውጭ ግንኙነት ክንውኖችን አብራረተዋል።
ከክንውኖቹ መካከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጉብኝት ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ክንውን እንደነበር ገልጸዋል። ልዑኩ ጉብኝት ባደረገባቸው ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ዑጋንዳ ከፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መምከሩንም አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ እየወሰደ ያለው የሕግ ማስከር ዘመቻ መነሻ፣ ይዘትና ዓላማ በዝርዝር ማስረዳቱን አብራርተዋል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ትህነግ የመንግስትን ሃገራዊ ሪፎርም ተቃውሞ፣ በተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች የሽብር አካላትን ሲደግፍ እንደነበር፣ በተደጋጋሚ የሕግ ጥሰቶች መፈጸሙንና በመጨረሻም በሃገር ሉዓላዊነት ቀይ መስመር ማለፉን የሃገራቱ መሪዎች እንዲገነዘቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህም መንግስት እየወሰደ ያለው ርምጃ የእርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር መሆኑን ማስረዳት ተችሏል ብለዋል አምባሳደር ዲና። የሃገራቱ መሪዎችም የኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነት ለአፍሪካ ቀንድ ሠላም መሰረት መሆኑን በመግለጽ፤ ሕግ የማስከበር ርምጃ የሃገር ውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ማንም ጣልቃ የሚገባበት እንዳልሆነ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት እየወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ንጹሃን እንዳይጎዱ ታሳቢ ተደርጎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቋማቸውን ማሳወቃቸውንም አክለዋል። በሕግ ማስከበር እርምጃው ንፁሃን እንዳይጎዱና ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይከሰት መንግስት ርምጃውን በጥንቃቄ እየወሰደ እንደሆነ ተገልጾላቸዋልም ብለዋል። አምባሳደሩ ከአራቱ ሃገራት በተጨማሪ ለሌሎች ጎረቤት ሃገራትም አሁናዊ ሁኔታዎችን የማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በጅቡቲና በሱዳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ማድረሳቸውንና ምክክር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። ጎረቤት ሃገራቱም ከኢትዮጵያ ሠላም ጎን መቆማቸውን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በፓስፊክ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላዎች እንዲሁም ግለሰቦች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁናቴ አስመልክቶ ለሃገራት መሪዎችና ሚዲያዎች ግልጽ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በመዲናዋ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተወካዮች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጻ እንደተደረገላቸውም እንዲሁ። በሌላ በኩል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ስለመቀጠሉ፣ በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ረገድም ከተለያዩ ሃገራት ኩባንያዎች ጋር የኢንቨስትመንት ምክክር መደረጉን ገልጸዋል። በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ከቤይሩት 83፣ ከጂዳ ከ280 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here