የምሥራቅ ኢትዮጵያ ታላቅ ገድል – ካራማራ!

94

ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለረጅም ዘመን በሀገሪቱ የነበረውን ዘውዳዊ ሥርዓት እንደ ቧልት ጥሎ ሥልጣን በድንገት የተቆናጠጠው ወታደራዊው መንግሥት መንበሩ ፈጽሞ አልረጋ ብሎታል፡፡ ለዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም ምክንያት የኾኑት ተራማጅ ተማሪዎች ውድ የኾነውን የሕይዎት ዋጋ ከፍለው ይወድቃል ተብሎ ያልታሰበውን ዘውዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ቢጥሉም ሥልጣኑን ባላሰቡት መንገድ ከእጃቸው ላይ የነጠቀው ወታደራዊ ክንፍ ክፉኛ ያበሳጫቸው ይመስላሉ፡፡

የተራማጅ ተማሪዎቹን የትግል ጥያቄ ጥያቄው አድርጎ ያስተጋባው የጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፤ ከውስጥም ከውጭም ተንኳሹ በዝቶበታል፡፡ ለዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር እንግዳ የኾነው የሀገሬው ሕዝብም በሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ እርግጠኛ መኾን ተስኖት ሁሉንም በትዝብት መመልከት ምርጫውም አማራጩም አድርጎ ዝም ብሏል፡፡

በዘመናት የሀገረ መንግሥት ስሪቱ “መሪ ከፈጣሪ” ብሎ የሚያምነው እና የኖረው ሕዝብ ተራማጆቹም፤ ወታደሮቹም የሚሉት ግራ አጋብቶታል፡፡ ወቅቱን የከፋ ያደረገው ደግሞ ጽንፍ የረገጡ ብሔርተኞች ከዚህም ከዚያም ብቅ ብቅ ማለታቸው ነበር፡፡ ጣሊያን የዘራችው እና የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያሳደጉት የከፋፍለህ ግዛ መርህ “የብሔር እኩልነት” የሚል ስያሜ ተችሮት አደገ፡፡

አክራሪ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት የላቀ ትኩረት ይዞ ንጉሠ ነገሥቱን አልፎ ስልጣን በአቋራጭ የያዘውን የማኅበረ ሱታፌ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አራማጅን የደርግ መንግሥት ሰላም ነስቶታል፡፡ መስከረም 2 ቀን 1966 ዓ.ም ሥልጣን የያዘው ደርግ ክፉኛ አማረረን ያሉ የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ የአኹኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቂት ተማሪዎች በወርኃ የካቲት ወደ ጫካ መግባትን ምርጫቸው አደረጉ፡፡

በዚህ መካከል ነበር ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት የቀደመ ራዕይ የነበራቸው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ብቅ ያሉት፡፡ ቀድሞውንም ታላቋን ሶማሌን የመመሥረት ንቅናቄ እንዳለ ቢታወቅም የኢትዮጵያን ወቅታዊ አለመረጋጋት ያዩት እና በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ይፋ አወጡት፡፡ የኢትዮጵያን የውስጥ ተገንጣዮች ጉልበት ያደረጉት እና የውጭ ድጋፍ የነበራቸው ፕሬዚዳንቱ ድንበራችን አዋሽ ይደርሳል አሉ፡፡

ታላቋን ሶማሌን የመገንባት ጥረት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይኾን ጅቡቲን እና ኬኒያንም የሚነካ ቢኾንም በወቅቱ ሀገራቱ በቅኝ ግዛት ሥር የወደቁ በመኾናቸው ከቅኝ ገዢዎች ጋር ትከሻ መለካካት አያዋጣም ያሉት ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ፤ ኢትዮጵያ እና የፕሬዚዳንት መንግሥቱ መንግሥት ቢወረሩ ይሻላል የሚል አቋም ያዙ፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ዘመቱ፡፡

1969 ዓ.ም የተጀመረውን ወረራ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የሀገረ ኩባ ወታደሮች በተሳተፉበት አውደ ውጊያ፤ የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬን ጦር ካራማራ ላይ ድል አደረጉት። ታላቋን ሶማሊያን የመመስረት ጥረት የነበራቸው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬም ሀገሪቱን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ላላባራ ጦርነት ዳርገዋት አለፉ፡፡
እነሆ የምስራቅ ኢትዮጵያ ታላቁ ገድልም ዛሬ 45 ዓመታትን አስቆጠረ፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!