የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን ኢትዮጵያ ያካሄደችው ምርጫ የተረጋጋና ሰላማዊ ድባብ የተላበሰ መሆኑን እንደታዘበ ገለጸ።

0
64

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን ኢትዮጵያ ያካሄደችው ምርጫ የተረጋጋና ሰላማዊ ድባብ የተላበሰ
መሆኑን እንደታዘበ ገለጸ።
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ ያካሄደችው ጠቅላላ ምርጫ በአብዛኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች
የተረጋጋና ሰላማዊ ድባብ ተላብሶ መካሄዱን ታዝቤያለሁ” ሲል የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን ገለጸ።
ቡድኑ ትናንት በአራት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በ190 የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ የምርጫውን ሂደት መታዘቡን
ገልጿል።
በዚህ መሰረት ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርት ከምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ መከፈት፣ የምርጫ ሂደት፣ የመዝጊያና ቆጠራን
ማዕከል አድርጎ ባደረገው የመታዘብ እንቅስቃሴ የምርጫ ሂደቱ በአመዛኙ ሰላማዊ ሁኔታን የተላበሰ እንደነበር ገልጿል።
የምርጫ ታዘቢ ቡድኑ ኃላፊ አምባሳደር አብዱላሂ አውላ አሊ እንደገለጹት፤ ሂደቱ በጠንካራ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የታጀበ፣ ንቁ
የሲቪክ ማኅበረሰብ ተሳትፎ የታየበት ነበር።
የምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ የመከፈት ሂደቱም ቡድኑ ከተመለከታቸው ጣቢያዎች 81 በመቶ የሚሆኑት በታቀደው ሰዓት መሠረት
የተከፈቱ ናቸው ብለዋል።
የምርጫው ቁሳቁስ ሥርጭቱም በአመዛኙ በቂ ቢሆንም የተወሰነ እጥረት ማጋጠሙን መታዘባቸውንም ጠቁመዋል።
“የተሻለ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ መታየቱ የሚበረታታ ተግባር ነበር” ብለዋል።
በጥቅሉ በቡድኑ ቅኝት በተደረገባቸው አካባቢዎች አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ በሰላማዊ ድባብ ውስጥ ሆኖ የተካሄደ መሆኑን
ገልጸዋል።
ከመራጮች ብዛት ጋር ተያይዞም የተደረገው የሰዓት ጭማሪ ውሳኔ ሚዛናዊነት የተላበሰ እንደነበረም አንስተዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ሁኔታውም ሲቃኝ በርካታ ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጎ ቢታይም ርቀትን በመጠበቅ
ረገድ ችግሮች እንደነበሩም ጠቅሰዋል።
አምባሳደር አብዱላሂ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ መደረግ ቢችሉ የተሻለ ነበር ያሏቸውን ተጨማሪ ጉዳዮችም አንስተዋል።
ከእነዚህም መካከል በተለይም ምርጫ ቦርድ የመራጮች ትምህርት ሰፋ ባለ መልኩ ቢሰጥ መልካም ነበር ነው ያሉት።
የቡድኑ ምክትል ኃላፊ ሊና ሁዋዎም ከመገናኛ ብዙኃን በአንዳንድ አካባቢዎች ግርግር መኖሩን በመጥቀስ ተጠይቀው ነበር።
እሳቸውም ሲመልሱ ቡድኑ ባደረገው ቅኝት ምንም አይነት ግርግርም ሆነ ሁከት አለማየቱንና በቢሾፍቱ ከተማ ብቻ የመራጮች
ቀላል መገፋፋት ተመልክቷል ብለዋል። ይህም የምርጫ ሂደቱ ላይ ምንም ተጽዕኖ በማይፈጥር መልኩ ወዲያው በጸጥታ አካላት
ቁጥጥር ሥር መዋሉንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከታዛቢዎቹ መካከል አሊ ሰኢድ አሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራቸው የተቃና እንዲሆን ላደረገው ትብብር ምስጋና
ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m