የሜካናይዜሽን ግብርና ተግባራዊ በማድረጋቸው ምርታቸው በእጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

0
176

እስከዚህ ወቅት ከ30 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሜካናይዜሽን መታረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል::

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሜካናይዜሽን ግብርና ተግባራዊ በማድረጋቸው በበሬ ያርሱ በነበሩበት ወቅት ያገኙ ከነበረው ምርት በእጥፍ መጨመሩን በወምበርማ ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡ በበሬ ሲያርሱ በነበሩበት ወቅት ስንዴ በሄክታር እስከ 25 ኩንታል ያገኙ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ግብርና ከጀመሩ በኋላ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

እስከ 40 ኩንታል በሄክታር ይገኝ የነበረውን በቆሎ ደግሞ እስከ 100 ኩንታል ማግኘት እንደቻሉ ነው አርሶ አደሮች የገለጹት፡፡ በተናጠል በራሳቸው የሚያርሱ አርሶ አደሮች ቢኖሩም አብዛኛው አርሶ አደሮች ግን በተመጣጣኝ ዋጋ በኩታገጠም እንደሚያሳርሱ ነግረውናል፡፡ በቆሎ፣ ስንዴ፣ በርበሬ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ ሰብሎችን በብዛት እንደሚያመርቱም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጅ በመኸር ወቅት ‘የኮምባይነር’ ችግር በማጋጠሙ በወቅቱ ለመውቃት እንደሚቸገሩ ነግረውናል፡፡ የመውቂያ ኮምባይነር ማሽንም ከሌሎች አካባቢዎች በደላላ በከፍተኛ ወጭ እንደሚያስመጡ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የእርሻ ትራክተሮች በወቅቱ ይቀርቡላቸው እንዳልነበር የገለጹት አርሶ አደሮቹ በዚህ ዓመት ግን ችግሩ መፈታቱን ነግረውናል፡፡
በምዕራብ ጎጃም የወምበርማ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘላለም ጌታሁን እንደገለጹት በወረዳው በባለፈው ዓመት 9 ሺህ ሄክታር መሬት በሜካናዜሽን ታርሶ ነበር፣ 12 ሺህ አርሶ አደሮች ደግሞ ተሳትፈዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 10 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዷል፣ 12 ሺህ 100 አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በዚህ ወቅትም ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ 680 ሄክታር መሬት በላይ መታረሱን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ 28 ትራክተሮችም በወረዳው እርሻ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በአማራ ክልል የግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አለባቸው አሊጋዝ እንደገለጹት ደግሞ በክልሉ ለሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት የሚውሉ 682 ትራክተሮች ከተለያዩ ተቋማት መኖራቸው ተለይቷል፡፡ ከተለዩት ውስጥም በዚህ ወቅት 208 ታራክተሮች የእርሻ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
እስከዚህ ወቅትም 30 ሺህ 712 ሄክታር መሬት መታረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ 21 ሺህ 55 አርሶ አደሮችም ተሳትፈዋል፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የቢራ ገብስ እና ማሽላን ጨምሮ 11 ሰብሎች በኩታ ገጠም በትራክተር የሚለሙ የሰብል ዓይነቶች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በክልሉ የምዕራብ ጎንደር የሜካናይዜሽን እርሻ ቀዳሚው ሲሆን ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋም ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ አለባቸው ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የሜካናይዜሽን እርሻ አርሶ አደሩ በበሬ በተደጋጋሚ ለማረስ የሚያወጣውን ድካም ይቀንሳል፡፡ በጥልቀት ስለሚታረስ ውኃና አየር ስርገት ስለሚጨምር አረምና በሽታን ይቀንሳል፤ ምርታማነትንም ይጨምራል፡፡

በመኸር ወቅት የሚያጋጥመውን የእህል መውቂያ ‘ኮምባይነር’ ችግር ለመፍታት ባለሀብቶች ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገቡ እየተሠራ እንደሚገኝም ነግረውናል፡፡

በክልሉ ከሚለማው ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 70 በመቶው በትራክተር ለማረስ ምቹ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

ፎቶ፡- ወንበርማ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ገጽ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here