የማኀበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ሥርዓት ግንባታ እና አተገባበርን የተመለከተ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው።

48

አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኮንፈረንሱን አስመልክቶ የኢፌዲሪ ሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመግለጫው እንዳሉት በኮንፈረንሱ ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የተውጣጡ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ይታደማሉ፡፡ የማኀበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች አተገባበር እና ሥርዓት ግንባታን የሚያሳዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በተጋበዙ ባለሙዎች ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባል ተብሏል፡፡

የማኀበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች በተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት የሚተገበሩ በመኾናቸው አቀናጅቶ ለመምራት እና አፈጻጸሙን ለማሳደግ ብሔራዊ የማኀበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ተቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል ሚኒስትሯ። የማኀበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መኾን እና በየጊዜው በሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት አፈጻጸም ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፖሊሲውን እና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂውን በሚገባ በመተግበር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ የማኀበራዊ ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ወሳኝ እንደኾነ ይታመናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም መስሪያ ቤቱ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያውን ሀገራዊ የማኀበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ ማካሄዱን ያስታወሱት ዶክተር ኤርጎጌ ተቋርጦ የነበረውን ኮንፈረንስ ለማስቀጠል “ማኀበራዊ ጥበቃ ለሀገር ግንባታ በኢትዮጵያ“ በሚል መሪ መልዕክት ከግንቦት 15 እስከ 16/ 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አዳራሽ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።

የኮንፈረንሱ ዋና ዋና ዓላማዎች፦

👉 አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የማኀበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን በማሳደግ ሥርዓትን የመገንባት አስፈላጊነትና ጠቀሜታውን በማሳወቅ የተለያዩ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ

👉 የማኀበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ግንባታንና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የሚያግዙ ምክረ ሀሳቦችን ለማመንጨት እንዲሁም የማኀበራዊ ጥበቃ ሽፋን እና ጥራትን ለማሳደግ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ ኀብረተሰቡ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊያበረክቱት ሰለሚችሉት አስተዋጽዖ ለመነጋገር

👉 የማኀበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ለመገንባት ለምናደርገው ጥረት በኮንፈረንስ ከሚቀርቡ የተለያዩ ጹሑፎችና መልካም ተሞክሮችን ለመቀመርና ለፖሊሲ እና ስትራቴጂ ክለሣ ግብዓቶችን ለማግኘት ነው።

👉የኮንፈረንሱን ሂደት በመገናኛ ብዙኃን በማስተላለፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የግል ክፍለ ኢኮኖሚው ላይ የሚሠሩ እና መላው ኀብረተሰብ በማኀበራዊ ጥበቃ ላይ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው እና ለቀጣይ ትግበራ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ

በአጠቃላይ በኮንፈረንሱ የተለያዩ አካላትን ግንዘቤ በማሳደግ በቀጣይ ሁሉም አካላት ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስቻል ሲሆን በተጨማሪም ዜጎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እነዚህ አካላት የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ይጠበቃል ተብሏል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!