”የማሕበረሰቡን ጤንነት ያረጋግጣል ያልነው የጤና መድሕን ዋስትና ችግሮች አሉበት” የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

0
48

”የማሕበረሰቡን ጤንነት ያረጋግጣል ያልነው የጤና መድሕን ዋስትና ችግሮች አሉበት” የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን ግለሰቦች አስቀድመው በሚያዋጡት
አነስተኛ ገንዘብ ከቤተሰብ አባል ቢታመም ያለ ስጋት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና የሚያገኙበት ሥርዓት ነው። መደጋገፍ፣
ፍትሐዊነትና አሳታፊነት ደግሞ መርሆቹ ናቸው።
አብመድ በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ሽና ጽዮን ቀበሌ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን አነጋግሯል። አቶ ጥጋቡ አክሎግ
የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድሕን በወረዳው ከተተገበረ ጀምሮ ከአምስት ቤተሰቦቻቸው ጋር አባል በመሆን አገልግሎቱን
በማግኘት ላይ ይገኛሉ። የጤና መድሕን አባል በመሆናቸው ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁ ህክምናዎችን በአባልነት ባዋጡት መዋጮ
ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው አቶ ካሳው አበበ የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባት ቤተሰቦቻቸው ጋር የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና
መድሕን አባል በመሆን አገልግሎቱን እያገኙ እንደሚገኙ ነግረውናል። ይህም ከዚህ በፊት እስከ ጎንደርና ባሕር ዳር ሆስፒታሎች
በመጓዝ ያወጡ የነበረውን ወጭ አስቀርቶላቸዋል። ለዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል ትኩረት መሰጠቱ ማሳያ እንደሆነም
ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ ”የማሕበረሰቡን ጤንነት ያረጋግጣል ያልነው የጤና መድሕን ዋስትና ችግሮች አሉበት” ነው ያሉት አቶ ካሳው፡፡
በሕክምና መሥጫ ተቋማት በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እና ምርምራ እንደማያገኙ ነግረውናል። “አንዳንዴም አቅርቦቱ ከተቋሙ
እያለ ጭምር ውጭ ከሚገኝ የግል ተቋም መድኃኒት እንድንገዛ እና ምርመራ እንድናደርግ ይደረጋል” ብለዋል። ይህ ደግሞ
ወጭው ከመንግሥት ተቋም ከእጥፍ በላይ ስለሚጨምር ህክምናውን ሳያገኙ እንደሚመለሱ ገልጸዋል።
መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ከሙያው ሥነ ምግባር ውጭ በሚሠሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም
ተናግረዋል። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ከግል ተቋማት የገዙትበን ገንዘብ “በጀት የለም” በሚል ተቋሙ ሊመልስላቸው
አለመቻሉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተጠቃሚዎች ነግረውናል።
የሽና ጽዮን ቀበሌ ሥራ አስኪያጅ መላኩ ገብሬ እንደገለጹት በጤና ተቋማት በቂ የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ተጠቃሚዎች
የግል መድኃኒት ቤቶች ላይ እንዲገዙ ይደረጋል።
በወረዳው የጤና መድሕን ሽፋን ዝቅተኛ በመሆኑ ታካሚዎች የከፈሉበትን ገንዘብ ለማስመለስ ተቸግረዋል ብለዋል። የወረዳው
አመራር ትኩረት ዝቅተኛ መሆን የአባላትን ሽፋን ለማሳደግ አለመቻሉንም ገልጸዋል።
የሊቦ ከምከም ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን ቡድን መሪ ሙላት አሰፋ እንደገለጹት ጤና
መድሕን በወረዳው 2007 ዓ.ም ጀምሮ የአገልግሎት ክፍያ ጀምሯል። ይሁን እንጅ የሚጠበቀውን አባል ማፍራት ባለመቻሉ
ተገቢውን ገቢ ሰብስቦ አገልግሎቱን መስጠት አስቸግሯል ብለዋል።
ከዓመት በላይ ያወጡትን ወጭም መመለስ አልቻለም። በዚህ ወቅትም ከ4 ሚሊዮን 347 ሺህ ብር በላይ ያልተከፈለ እዳ መኖሩን
ቡድን መሪው ገልጸዋል። ይህ ደግሞ አባላትን ለማፍራት ትልቅ ችግር ፈጥሯል። በዚህ ወቅት በወረዳው የጤና መድሕን አባል
ሽፋን 60 በመቶ መድረስ ሲገባው ማከናወን የተቻለው 45 በመቶ ብቻ ነው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን ቡድን መሪ አወቀ ፈይሳ የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን
በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች
የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን አባላት ቁጥር አነስተኛ መሆንና የጤና ተቋማት ለሰጡት አገልግሎት ቶሎ ክፍያ ባለመፈጸሙ
የመድኃኒት አቅርቦት ችግር አጋጥሟል።
በዚህም ምክንያት ታካሚዎች መድኃኒት ከግል ተቋማት እንዲገዙ ይገደዳሉ። የግል ተቋማት የዋጋ መጋነን ደግሞ ታካሚዎችን
ለችግር፣ መንግሥትን ደግሞ ለኪሳራ እየዳረገ ይገኛል። በዚህም ዞኑ በስድስት ወሩ 46 ሚሊዮን ብር ዕዳ መግባቱን ቡድን
መሪው ገልጸዋል። ችግሩን ለክልሉ መንግሥት ማሳወቃቸውንም ነው አቶ አወቀ የገለጹት።
የአባላትን ቁጥር ለማሳደግና የአባላትን ክፍያ ለማሻሻል ጤና መምሪያው ከጤና ቢሮ እና ከጤና መድሕን ኤጀንሲ ጋር በመሆን
ጥናት ለማካሄድ አቅጣጫ መቀመጡንም ቡድን መሪው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here