የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ዉሳኔዎች አሳለፈ፡፡

0
467

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ዉሳኔዎች አሳለፈ፡፡

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ዉሳኔዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ የልማት ዕቅድ ፍኖተ ብልጽግና 2013 እስከ 2022 ሰነድ ላይ ተወያይቷል፡፡
የልማት መሪ ዕቅዱ ሃገር በቀል የእድገት አቅጣጫን የተከተለ፣ በዘርፎች መካከል ሊኖር የሚገባው ትስስር የሚያጎለብት፣ የቀጣይ አስር ዓመታት የሚተኮርባቸውን የልማት ምሰሶዎች እና የትኩረት መስኮች በሚገባ የለየ፣ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ብሎም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ
ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቦ በልማት ዕቅድ ፍኖተ ብልጽግና 2013 እስከ 2022 ሰነድ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል አጽድቆ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡
የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚያረጋግጠጥ፣ የመገናኛ ብዙኃን በተቋምነታቸው የአሰራር ነፃነት እንዲኖራቸው እና የሃሳብ ብዝሃነትን የማስተናገድ አቅም እንዲያጎለብቱ የሚያስችል ሁሉንም አይነት የሚዲያ ዘርፎች በወጥነት በአንድ የህግ ማእቀፍ ማስተዳደርና መቆጣጠር የሚያስችል፣ የቴክኖሎጂ እድገት የደረሰበትን የሚዲያና ብሮድካስት ቴክኖሎጂ እውቅና የሚሰጥ፣ በገለልተኝነት ዘርፉን የሚመራ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋማዊ ስርዓት ማጎልበት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ