‹‹የመንፈስ እና የሞራል ልዕልና እየኮሰሰ፣ የቁስና የገንዘብ ልዕልና በመግነኑ እየገጠሙን ላሉ ችግሮች ምክንያት ሆኗል››

247
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
‹‹የመንፈስ እና የሞራል ልዕልና እየኮሰሰ፣ የቁስና የገንዘብ ልዕልና በመግነኑ እየገጠሙን ላሉ ችግሮች ምክንያት ሆኗል››
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 12/ 2013 ዓ.ም (አብመድ) ከሳይንስ የሚገኘው ዕውቀት በአብዛኛው ለዕድገት የሚረዳ እንጅ ሰውን መልካም የማድረግ ሚናው ዝቅተኛ እንደሆነ የግብረገብ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ዶክተር ጠና ደዎ ሰው፣ ግብረገብና ሥነ ምግባር በሚል ባሳተሙት መጽሃፍ የተማረ ሰው የተሻለ የሚሆነው በዕውቅት እና በክህሎት ባቻ ሳይሆን በባህሪም ጭምር ነው፡፡ ዕውቀት እና ክህሎት ብቻውን ስብዕናን አያላብስምና፡፡ ለቁሳዊ ነገሮች የሚሰጥ ዋጋ የግብረ ገብ አቅምን አዳክሞታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ከፍተኛ የሥነ ምግባር እሴት ቀውስ ይታያል፡፡ የቀውሱ ምክንያት በአንድ በኩል የቁሳዊ እሴቶች ጠቀሜታ እጅግ የተጋነነ ትኩረት ስለተሰተጠው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ግብረ ገብ፣ ስነ ውበትና መንፈሳዊ እሴቶች ትኩረት አለማግኘታቸው እንደሆነ ዶክተር ጠና ደዎ አሰፍረውታል፡፡
ግብረ ገባዊ እሴቶችን እና ሕግጋትን በመቅረጽ፣ በማስከበር፣ በማወቅ እና በማሳወቅ፣ በመቀበል፣ በመረከብ እና በማስቀጠል ቤተሰብ፣ የመንግስትና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ቤተ ዕምነቶች ከፍተኛ ሚና ያላቸው ማሕበራዊ ተቋሞች ናቸው፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ መምህር እና የቀድሞ የግብረገብ መምሕር አባ በዓማን ግሩም ለቁሳዊ እሴቶች የተሰጠው ትኩረት ለግብረ ገብ እሴት መቀጨጭ ትልቅ ምክንያት ሆኗል የሚለውን ሀሳብ ይጋሩታል፡፡ ይህም ‹‹የመንፈስ እና የሞራል ልዕልና እየኮሰሰ፣ የቁስና የገንዘብ ልዕልና መግነኑ የግብረ ገብ እሴት መቀጨጭን አሰከትሏል›› ብለዋል፡፡
አባ በአማን እንደገለጹት ሌላው ምክንያት እንዳለ ሁኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙት ግድያዎች እና ግጭቶች የግብረ ግብ መውደቅ ማሳያ ናቸው፡፡ የግብረ ግብ ችግርን ማስተካከል የሚችል ባለቤት አለመኖሩ ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ወንጀሎች እንዳይከሰቱ የግብረገብ እሴቶችን ማስተማር ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለ አባ በዓማን አስገንዝበዋል፡፡ ችግሩንም ተቋማዊ መዋቅር በመዘርጋት መፍታት እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡
በሀገራችን ያለውን የግብረ ገብ መቀጨጭ ለማስተካከል ከቤተሰብ እና ከሃይማኖት ተቋማት ባለፈ መንግስት ግብረ ገብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ የትምህርት ስርዓታችንም ሀገር በቀል መሰረት እንዲኖረው እና የግብረ ገብ ትምህርት ሊያካትት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ በግብረ ገብ የተገነባ ትውልድ መፍጠር ካልተቻለ ሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ሊገጥማት እንደሚችልም አባ በዓማን አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here