የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሚያዝያ 4 ጀምሮ የመንግሥት ንብረት ምዝገባ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

0
103
የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሚያዝያ 4 ጀምሮ የመንግሥት ንብረት ምዝገባ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን የግዥ አፈፃፀምና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊነትን መከታተል፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ማድረግ እና በሕግና በአፈፃፀም ሥርዓቱ ላይ የማሻሻያ ሀሳቦች ማቅረብ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ቀዳሚ ኀላፊነቱ ነው፡፡
ኤጀንሲው በአዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 15 ላይ በተሰጠው ኀላፊነት ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ የወጣባቸው ነገር ግን ያለአገልግሎት የተከማቹ የመንግሥት ንብረቶች ምዝገባ ለማከናወን እና በቀጣይም የሚወገዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከሚያዝያ 4 እስከ 8/2013 ዓ.ም ጀምሮ ሀገራዊ የንብረት ምዝገባ ሳምንት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማከናወኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሐጅ ኢብሳ አስታውቀዋል፡፡
ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለመፍጠር አጋዥ ነው በተባለው በዚህ የንብረት ምዝገባ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ 31 ግብረኀይል በማዋቀር የቅድሚያ ምዝገባ ሥራውን ማጠናቀቁን እና ለተፈጻሚነቱም 190 ለሚደርሱ የመንግሥት ተቋማት በደብዳቤ አሳውቋል። ኤጀንሲው “ሥራው ተሞክሮዎች የተወሰዱበት ነው” ብሏል፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀ እና መግባታቸውም ሆነ መወገዳቸው ያልታወቁ ንብቶች መኖሩ እየታወቀ በቀናት ውስጥ ሥራው እንዴት ይጠናቀቃል እንዲሁም በምዝገባው የተገኙ የኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክምችቶች ግኝት ላይ የሀብት ሽግሽግ ለማድረግ ምን ታስቧል? ሲል አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጠይቋል፡፡
የሚካሄደውን ምዝገባ ተከትሎ አጠቃላይ ሥራ ላይ ያሉ፣ የተበላሹ እና በከፊልና በአጠቃላይ የሚወገዱ ንብረቶችን ካወቅን በኋላ ፍትሐዊነትን በተከተለ መልኩ የሚወገዱ ንብረቶች ተለይተው ይወገዳሉ፤ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ትርፍ ሀብቶችን ለሌሎች የማከፋፈል ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያው ላይ ከፍተኛ ውድመትን ሊያስከትል የሚችል አደገኛ የኬሚካል ክምችት ማግኘቱን አሰታውቆ ይህን ለማስወገድ የሌሎች ሀገራት የኬሚካል አወጋገድ ጥናት ተጀምራል ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here