ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን የለውጥ ትግበራ አፈጻጸምን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ ገብቷል። የተዘጋጁ መመሪያዎችን በተቋማት ለመተግበርና ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲቻል በክልሉ ለሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ለስድስት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ.ር) በማጠናቀቂያ መርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የሥራ ሥምሪት ሰጥተዋል። የሥራ ሰዓትን ያለማክበር እና በቢሮም ተገኝቶ ተገቢውን አገልግሎት ያለመስጠት ችግሮች እንደሚስተዋሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ጌታቸው አንስተዋል።
የክልሉን እምቅ ሃብት ለማልማትና የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የመንግሥት ሠራተኛው በተለይም ደግሞ የሥራ ኀላፊዎች በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም ገልጸዋል። በማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን እና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታትም የመንግሥት ሠራተኛው ግንባር ቀደም ኾኖ መገኘት እንደሚገባው አሳስበዋል። የመደማመጥ ባሕልን በማሳደግና አንድነትን በማጠናከር በክልሉ ልማት ላይ በጋራ ለመሥራት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ስልጠናው በዋናነት በካይዘን፣ በሥራ ሥነ-ምግባርና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ሥራ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት እንዲሁም ለውጥና ሥራን መገምገምና መለካት ላይ ያተኮረ ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!