እንጅባራ:የካቲት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በየአካባቢው የሚስተዋሉ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ችግሮችን ለመፍታት የምክር ቤት አባላት ሕዝባዊ ውክልናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ፡፡
የአዊ ብሔረሰብ ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 26ተኛ መደበኛ ጉባዔውን በእንጅባራ ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ሙሉዓዳም እጅጉ በሀገራችን የሚታየውን አንፃራዊ ሠላም በመጠቀም የሕዝቡን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየአካባቢ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳድር ችግሮችን የሕዝብ ወኪሎች በአግባቡ መፍታት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በተለይም ሕገ ወጥ ተግባራትን መከላከል ፣በብሔረሰብ አሥተዳድሩ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በተገቢ መንገድ ማልማት፣የልማት ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን፣ የጤና፣የገቢ አሰባሰብ እና ሌሎች ሥራዎችንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በጉባዔው የሴክተር መሥሪያ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!