“የሕግ የበላይነት መከበር እና መልካም አሥተዳደር መስፈን ለአስተማማኝ ሰላም፣ ለግጭት አፈታት እና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ናቸው” ዶክተር ዘውዱ እምሩ

160

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት አዘጋጅነት ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
“መልካም አሥተዳደር እና የሕግ የበላይነት ለግጭት አፈታትና ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ያለው አውደ ጥናት ወቅታዊ እና ሀገራዊ ትርጉም ባላቸው ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የጥናት ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡
የሕግ ትምህርት ቤቱ ለውይይት ያቀረባቸው የጥናት ጽሑፎች እና ርእሰ ጉዳዮች ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ለኢትዮጵያ ያስፈልጓታል ያሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጂክ ኮምዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ አሁን ላይ በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ ከመልካም አሥተዳደር እና የሕግ የበላይነት ችግሮች የመነጩ ናቸው ብለዋል ዶክተር ዘውዱ፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሕግ የበላይነት እጅግ አስፈላጊ የሚኾንባቸው ሦስት መሠረታዊ ነጥቦች እንዳሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
መልካም አሥተዳደር እና የሕግ የበላይነት መከበር የድኅረ 2015 ዘላቂ ልማት ግቦች መካከል አንዱ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር እና መልካም አሥተዳደር መስፈን ለአስተማማኝ ሰላም፣ ለግጭት አፈታት እና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መከበር በዓለም ጀስቲስ ፕሮጀክት ከ139 ሀገራት 122ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ እና ከ33 የአፍሪካ ሀገራት 27ኛ መገኘቷ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
የመልካም አሥተዳደር እና የሕግ የበላይነት መከበር በኢትዮጵያ ወቅታዊ እና ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ተገኘ ዘርጋው ናቸው፡፡
የአውደ ጥናቱ ዓላማም በሕግ የበላይነት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጥንቶ ለአስፈጻሚው አካል በምክረ ሐሳብ ደረጃ ማቅረብ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ተገኘ ተቋማት ሕግና ሥርዐትን አክብረው መሥራት ግዴታቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝብ በእነዚህ ተቋማት መገልገል ደግሞ መብቱ መኾኑን ማወቅ ተገቢ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የሕግ የበላይነት አለመከበር ችግርን መፍትሔ ለመሻት የኹሉንም ዜጎች ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ እንደኾነ ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ ያነሱት፡፡
ሌላው በአውደ ጥናቱ በጥልቀት የተነሳው ጉዳይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሽብር ቡድኑ ትህነግ ከከፈተው ጦርነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው የውጭ ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እየተስተዋለ ያለው ጣልቃ ገብነት እና ጫና ዓለም አቀፋዊ ሕግን የጣሰ እንደኾነ ረዳት ፕሮፌሰር ተገኘ አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች የሚስተዋለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በጥናት ታግዞ መሞገት የምሁራን ድርሻ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
እየተካሄደ የሚገኘው አውደ ጥናት ዓላማውም የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚሞግት የምሁራን ተሳትፎን ማሳደግ ጭምር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/