ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በህገ ወጥነት እና በጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶች ላይ ወጥ የሆነ አቋም በመያዝ ፊት ለፊት መጋፈጥ ይገባል ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።
ከግንቦት 10/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ በተካሄደው የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።
የሕዝብ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን አመራሩ እንደየሚመራው ተቋም እና አካባቢ ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ መስጠት አለበት ያሉት አቶ ተመስገን አመራሩ የራሱን ድርሻ ባለመወጣት አሻግሮ መመልከትና በውጫዊ ችግር ታጥሮ ኀላፊነቱን ያለመወጣት ድክመቱን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው ለሕዝብ ተደራሽና ችግር ፈቺ አገልግሎት ከማጉደል ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል። አመራሩ ከተለያዩ የሌብነት፣ ብልሹ አሠራሮች እና ሰርጎ ገብነት ከመሳሰሉ ኋላ ቀር ድርጊቶች መውጣት አለበት ብለዋል።
የክልሉን ሕዝብ ስነ ልቦና፣ ባህል እና ከፍታ የሚመጥን አመራር የመፍጠር አቅጣጫን በመከተል ለሚመራው ሕዝብ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበትም አመላክተዋል።
ከለውጡ ወዲህ ከፍተኛ የሆኑ ሥራዎች መሠረታቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን “በለውጡ ዓመታት በርካታ ድሎች ተገኝተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ እየታዩ ያሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን ሲገመግም የቆየው የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ ዛሬ አመሻሽ ላይ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!