“የልደት በዓልን በላል ይበላ ማክበር የተለየ ስሜት እና ድባብ አለው” የውጭ ሀገር ጎብኝዎች

56
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከወትሮው ምዕራባዊያን ጎብኝዎች እና ሩቅ ምሳራቃዊ አሳሾች ከስፍራው አይርቁም ነበር፡፡ ዓመቱን ሙሉ እንግዳ ነጥፎበት የማያውቀው ላል ይበላ እና አካባቢው በተለይ ደግሞ በወርሃ ታህሳስ መገባደጃ ላይ እንግዶቹ ይበዛሉ፡፡
በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ድምቀት ከሚከበሩ ሐይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አንዱ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት የልደትን በዓል በላል ይበላ ለመታደም ከዓለም ክፍል የሚመጡ ምዕመናን እና ጎብኝዎች የበዓሉ ውበት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴው ድምቀት ነበሩ፡፡
የልደት በዓል በላል ይበላ እና አካባቢው ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በተጨማሪ ከቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እስከ ዐርባቱ እንስሳት፣ ከብልብላ ጊዮርጊስ እስከ ብልብላ ቂርቆስ፣ ከሳርዝና ቅዱስ ሚካኤል እስከ አቡነ ዮሴፍ፣ ከቅዱስ ነአኩቶለአብ እስከ አሸተን ቅድስት ማሪያም፣ ከገነተ ማሪያም እስከ ልደታ ማሪያም የማይጎበኝ ቅዱስ ስፍራ የለም፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአካባቢው ለዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ሕልውናዋ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ለተመሰረተው ላል ይበላ ከተማ ስጋት ሆኖባት ቆይቷል፡፡
የልደት በዓልን ከአንጻራዊ ሰላም ማግስት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴዎቿን አጠናቅቃ እንግዶቿን መቀበል የጀመረችው የላል ይበላ ከተማ የውጭ ጎብኝዎችንም መቀበል ጀምራለች፡፡ በልደት በዓል ከ12 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ይገባሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን የተወሰኑት ከበዓሉ ቀን ቀድመው ላል ይበላ ከተማ ደርሰዋል፡፡
ከእንግሊዝ ሎንዶን እንደመጣች የነገረችን ኮቻሌን ኢትዮጵያንም ላል ይበላንም ስትጎበኝ የመጀመሪያ ቢሆንም በርካታዎቹን እውነታዎች ከዩቱዩብ ላይ ቀድሜ ሰምቻቸዋለሁ ብላናለች፡፡ የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት፣ የሀገሪቱን ጥንታዊ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ባህል ቀድሜ ብሰማም ባየሁት ነገር ግን ተደምሜያለሁ ብላለች፡፡
የኢትዮጵያዊያን የልደት በዓል ከሚከበርበት ቀን ቀድሞ በላል ይበላ ከተማ ያለው የበዓል ድባብ እንደማረካት የነገረችን ጎብኝዋ የልደት በዓል የሚከበርበት ቀን እና የዋዜማውን ምሽት ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓት እስክታይ ድረስ እንደቸኮለችም አጫውታናለች፡፡
ሌላው እንግሊዛዊ ጎብኝ እና የፎቶ ግራፍ ባለሙያ እንደሆነ የነገረን ማክስ “የልደት በዓልን በላል ይበላ ማክበር የተለየ ስሜት እና ድባብ አለው” ብሏል፡፡ በላል ይበላ የሚከበረው የልደት በዓል በሌሎች ሀገራት ከሚስተዋለው የአከባበር ሥርዓት ፍጹም የተለየ ነው የሚለው ጎብኝው የሃይማኖቱ ተከታዮች ጽናት፣ እምነት እና የደስታ ስሜት ወደር የለለው እንደሆነ ይናገራል፡፡
በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የኪነ ህንጻ ጥበብ እና ውበት ሳስብ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ጠቢባን እንደነበሩ መገመት ቀላል ነው የሚለው የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ጎብኝ እስከ አሁን ድረስ ያለው ትውልድ ቅርሶቹን ጠብቆ ለትውልድ ማድረሱም የሚያስመሰግን ተግባር ነው ይላል፡፡
እጅግ ውብ እና ማራኪ በሆነው የኢትዮጵያውያን የቡና ሥርዓት ከበርካታ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተቀራርቦ የመጨዋዎት እድል እንደነበረው የነገረን ማክስ በእንግዳ ተቀባይነታቸው እና መልካም ሥነ-ምግባራቸው ተወዳጅ እና ትሁቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!