“የሊቃውንት መገናኛ፣ የደጋጎች መማፀኛ”

104
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሥፍራም ስፍራ ይመረጣል። ከስጦታም የላቀ ስጦታ ይሰጣል፣ ከውበትም ውበት ይበልጣል፣ ከግርማም የላቀ ግርማ ይኖራል፣ ከክብርም የከበረ ክብር አለ። ከፀጋም የላቀ ፀጋ አለ። ጅራፍ አይጮህባትም፣ ተናካሽ እንስሳት አይናከሱባትም፣ በግዝት ታሥረው፣ በትእዛዝ ተይዘው ይኖራሉ እንጂ። ተናካሽ እንስሳት ቃል ኪዳንን አክብረው፣ በአበው ትዕዛዝ ተገዝተው ይኖራሉ፣ የእንስሳዊ ፀባያቸው ቃል ኪዳኑን አያስረሳቸውም፣ ትእዛዙን አያስታቸውም፣ ሕጉን አያስፈርሳቸውም፣ አበው እንዳሉት ይኖራሉ፣ የአበውን ቃል ያከብራሉ እንጂ። አምላክ በረከቱን አይነፍጋትም፣ ልምላሜ አያሳጣትም። አበው በጽሞና ይመላለሱባታል፣ የጽድቅን ነገር ይሠሩባታል።
የተጨነቁትን ታጽናናለች፣ የተቅበዘበዙትን ታረጋጋለች፣ የደከሙትን ታሳርፋለች፣ የራባቸውን ታጎርሳለች፣ የተጠሙትን ታጠጣለች፣ የመንፈስ ምግብ ትሰጣለች፣ የልብ እርካታ የሚሰጠውን የመንፈስ ውኃ ታጠጣለች። በአረንጓዴ ካባ እንደተዋበች ትኖራለች። ብዙዎች ሲራቆቱ፣ ብዙዎች ወዘናቸው ሲጠፋባቸው፣ ያጌጡበት ካባቸው፣ የተዋቡበት ጌጣቸው በረገፈባቸው ጊዜ እርሷ ግን ከእነውበቷ ትታያለች፣ ከእነ ጌጧ ትኖራለች። የማያረጅ ውበት፣ የማይለቅ ጌጥ ሰጥቷታልና።
በዚያች ሥፍራ ያልተደረሰባቸው ታሪኮች፣ ያልተከፈቱ የምስጢር ቁልፎች፣ ያልታዩ የጥበብ ምንጮች፣ ጥበብን የሚነግሩ አባቶች፣ በደግነት የሚኖሩ እናቶች ሞልተዋል። በዚያች ሥፍራ ትዕዛዝ ይከበራል። በዚያች ሥፍራ ፈጣሪ ይፈራል፣ በዚያች ሥፍራ በበረከት ይኖራል፣ በዚያች ሥፍራ እውነተኛው ታሪክ ይነገራል፣ በዚያች ሥፍራ ሃይማኖት ጸንቶ ኖሯል፣ በዚያች ሥፍራ ቃል ኪዳን ይፀናል። በዚያች ሥፍራ የሊቃውንት ጥበብ ይፈስሳል፣ የደቀመዛሙርቱን ልብ ያረሰርሳል።
ሊቃውንት ይገናኙባታል፣ ደጋጎች ይማፀኑባታል፣ ከአምላካቸው ረድኤት እና በረከትን ይቀበሉባታል። ትእዛዛትን ጠብቀው ያስጠብቁባታል። ኢትዮጵያ የምትገለጥበት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚከብርበት፣ ሃይማኖት የፀናበት፣ ታሪክ ከፍ ከፍ ያለባት ምስጢራዊ ሐይቅ ጣና ሞገስን የሰጣት፣ ውበትን ያጎናፀፋት፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ ከመወደድ ላይ መወደድ የደራረበላት ናት መልካሟ ምድር ዘጌ።
ፃዲቁ አቡነ በትረ ማርያም ጣናን በታንኳ ይሻገሩ ነበር። በሚሻገሩበትም ጊዜ በዘንጋቸው ይቀዝፉ ነበር። ሐይቁን አልፈው ከየብስ በደረሱ ጊዜ አባ በምን ተሻገሩ? ተባሉ። እሳቸውም በዘንጌ አሉ። ይህም ዘንጌ ያሉት ዘጌ ተብሎ ለዚያች ውብ ሥፍራ ስያሜ ሆነ ይባላል። ጥጋቡ ተፈሪ አኤልታማክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ዘጌ ለተሰኘው ስያሜ ሁለት አባባሎች አሉ ይላሉ። የመጀመሪያው በአንድ ዘመን የመከራ ዘመን ወይም ድርቅ መጥቶ ነበር። ያን ጊዜም ከኢየሩሳሌም የተላከ እህል ከሰማይ ይወድቅ ጀመር። በዚያም ጊዜ ከሰማይ ዘው፣ ዘግ አለ ተባለ። ይህም ዘግ አለ የሚለው ዘጌ ከሚለው ስያሜ መጣ ይባላል። ሁለተኛው ግን ከአቡነ በትረ ማርያም ጋር የተያያዘው እና በዘንጌ ያሉት ነው ይላሉ። አቡነ በትረ ማርያም በምን ተሻገሩ ሲባሉ በዘንጌ ያሉት ከመጀመሪያው ይልቅ ሚዛን የሚደፋ ከታሪክ ጋር የሚገናኝ ሥያሜ ነው ብለዋል።
ዘጌ ቃል ኪዳን የሚጠብቃት፣ ውበት የበዛላት፣ ፀጋ የተትረፈረፈላት፣ እርጋታና ሰላም ያለባት፣ ነብስ የምትደሰትባት፣ ሀሴትም የምታገኝባት ሥፍራ ናት። ዘጌ በአንድ ሕግና ሥርዓት የሚተዳደሩ ገዳማት ያሉባት፣ በሠርክ የአምላክ ሥም እየተነሳ ምስጋና እና ውዳሴ የሚቀርብባት፣ ከንቱዋን ዓለም የናቁ አበው የሚኖሩባት፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ቅርስ ያለባት ውብ ሥፍራ ናት። ዘጌ ፍጥረት ሁሉ የተረፈችባት፣ ኖኅ ዘርን በምድር ላይ ያስቀረባት፣ ቃል ኪዳን ተቀብሎ በቃል ኪዳን የተጠበቀባት፣ የአምላኩን ትእዛዛት ያከበረባት፣ አምላክ ጥበቡን እና ኃያልነቱን ያሳየባት፣ ዓለም የተቀጣችበት ንፍር ውኃ ያላጠፋት የኖኅ መርከብ ያረፈችባት አራራት ተራራም የሚገኝባት ናት ይላሉ አበው። በዚያች ሥፍራ ዓለም ከጥፋት በኋላ በኖህና በዘሩ፣ እርሱም በቃል ኪዳን ባተረፋቸው ፍጥረት እንደገና ጀምራለች። በዚያች ሥፍራ ቃል ኪዳን ፀንታለች። በዚያች ሥፍራ ኢትዮጵያ ዘር የተገኘባት፣ የበረከትና የሰላም ዘመንም የተጀመረባት መኾኗ የታየባት ናት።
በዚህ ውብና የተባረከ ሥፍራ በቀደመው ዘመን ከብት በእግሩ አይገባም ነበር ይባላል። ከብቶች ዘጌ ከመግባታቸው አስቀድሞ ታርደው ስጋቸው ይመጣ ነበር ብለውኛል ታሪክ አዋቂው ይሄዓለም አምባው። ዘጌ አትክልት ያለባት፣ አበው በባረኩትና በፈቀዱት የሚኖርባት ሥፍራ ናት። አበው ያስቀመጡት ቃል ኪዳንም ዛሬ ድረስ ፀንቶባት ይኖራል። በመልካሟ ምድር ተገኝቻለሁ። የበዙ መልካም ታሪኮችን ሰምቻለሁ፣ የተባረኩና የተቀደሱ ሥፍራዎችን አይቻለሁ፣ በዛፎች መካከል ባሉ የዥግራና የቆቅ መረማመጃ በሚመስሉ መንገዶች እየተረማመድኩ የከበረውን ነገር ተመልክቻለሁ።
የሐመረ ኖኅ ኡራ ኪዳነ ምህረት፣ የደብረ ስላሴና የምዕራፈ ቅዱሳን ዋሻ መድኃኔዓለም ገዳም አስተዳዳሪ አባ ሃይማኖት አናጋው የኖኅ መርከብ ባረፈባት ሥፍራ ላይ በዘጌ የሚገኙ ገዳማት የመስቀል በዓልን በጋራ እንደሚያከብሩበት ነግረውኛል። አራራት ቀደም ሲል ከንፍር ውኃ የተረፉ ፍጥረታት በመርከብ ያረፉባት፣ አሁን ደግሞ ገዳማቱ የሚገናኙባት እና አንድነት የሚፈጥሩባት ናት። በቀደመው ዘመንም በረዶ ምድርን እንዳይመታት፣ በሰዎች መካከል ፀብ እንዳይኖር በዘጌ የሚኖሩ ሰዎች ጸሎተ ምሕላ ያደርሱባት ነበር ይባላል። ጸሎተ ምሕላቸውም ይሰማላቸዋል። የጠየቁት ይሰጣቸዋል።
የዥግራና የቆቅ መንገዶች በሚመስሉት ቀጫጭን የዛፍ ሥር መንገዶች እየተጓዝኩ፣ ተፈጥሮን፣ ታሪክን እና ሃይማኖትን እያደነቅኩ በሐመረ ኖኅ ኡራ ኪዳነ ምህረት አፀድ ሥር ደርሻለሁ። ሐመረ ኖኅ ኡራ ኪዳነ ምኅረት እጅግ የተዋበች፣ ታሪክን ደራርባ የያዘች፣ የጠበቀች ቤተ መቅደስ ናት።
ሁለት ደጋግ ባልና ሚስት ነበሩ። የማነብርሃን እና ሐመረወርቅ የተሰኙ። በደግነት የኖሩ፣ አምላካቸውን የሚፈሩ፣ ትእዛዛቱንም የሚያከብሩ ነበሩ። እነዚህ ደጋግ ሠዎችም ከአብራካቸው መልካም ልጅ ተሰጣቸው። ስማቸውም ዮሐንስ ይባላሉ። እኒህ ከደጋግ ሰዎች የተገኙ ብላቴና በደግነት እና አምላካቸውን በመፍራት፣ ትእዛዛቱንም በመጠበቅ አደጉ። በየገዳማትና በየአድባራት ለጌታቸው ታማኝ አገልጋይ ሆነው ኖሩ። አምላክም በደገኛው አገልጋዩ ደስ ተሰኘ። በአንድ ወቅትም የእግዚአብሔር መላእክ እየመራ ወደ መልካሟ ምድር አደረሳቸው። ያችም ሥፍራ ዘጌ ነበረች። በዚያችም ሥፍራ ቤተመቅደስ ያንፁ ዘንድ ተፈቀደላቸው። ቤተ መቅደስም አነፁ። እየመራ ወደ መልካሟ ምድር ያደረሳቸውም መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነበር። ቤተ መቅደሱን ሠርተው ከጨረሱ በኋላም የደገኛውን መላክ ስም ለማስታወስ ሲሉ ኡራ ብለው ሰየሟት። ታቦቷም ከኢየሩሳሌም የመጣች ናት። ሐመረ ኖኅ ኡራ ኩዳነ ምህረት የታነፀችበት ዘመንም በአፄ አምደጽዮን ዘመን ነው ብለውኛል አባ ሃይማኖት።
በክብ ቅርፅ የታነፃችው ይህች ውብ ቤተክርስቲያን ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ አላት። በቅኔ ማሕሌቱ አርባ አራት አምዶች አሏት። ቅድስቷም አሥራ ሁለት በሮች እና አሥራ ሁለት መስኮቶች አሏት። በሮችም እጅግ ያማሩና በጥንት ዘመን የተሠሩ እንጨቶች ናቸው። መቅደሷም ሥስት በሮች እና ሦስት መስኮቶች አሏት። በዚያ ውስጥ ያለ ምክንያት እና ያለ ምልክት የተሠራ የለም። ሁሉም ምስጢር ሊመሰጠርበት፣ ሃይማኖት ሊሰበክበት፣ ታሪክ ሊነገርበት በጥበብ ተሠራ እንጂ። ያቺ ውብ ቤተመቅደስ እጅግ ባማረና በተዋበ ጥበብ የተሠራች ናት።
በዚያች ውብ ቤተመቅደስ እጅግ ያማሩ፣ የአበው ጥበብ እና ፀጋ ያረፈባቸው ስዕሎች ይገኛሉ። እነዚያ ጥንታዊ ስዕሎች ዛሬም የትናንቱን ጥበብ እየነገሩ፣ ሃይማኖትን እያስተማሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። አሁን ላይ ግን ከእድሜ መብዛት የተነሳ በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በረቀቀ ጥበብ የተሳሉት ስዕሎች የመጽሐፍ ቅዱስን፣ የገድላትና የታምራትን ታሪክ የሚገልጡና የሚያስተምሩ ናቸው።
በዚያች ቤተክርስቲያን ደናግላን ብቻ ቅዳሴ ይቀድሱባታል፣ ስጋ ወደሙ ይፈትቱባታል። በቤተክርስቲያኗ አጸድ ሥር በዝግታ እየተመላለስኩ ተመለከትኳት። የተዋበች ናት። ረጃጅም ዛፎች እያረገዱላት፣ አእዋፋት እየዘመሩላት፣ አበው አምላካቸውን እያመሰገኑባት ኖራለች። ትኖራለች። በዚያች ውብ ቤተ መቅደስ አጸድ ሥር ታሪክን የሚነገሩ፣ ሃይማኖትን የሚያስተምሩ እንቁ ንዋዬ ቅድሳት ይገኛሉ። ዘመናትን የተሻገረ ታሪክና የጥበብ አሻራዎች ከበዋታል። ወደዚያች ሥፍራ ያቀና ሁሉ ዓይኑ መልኳሟን ነገር ታያለች፣ ልቡ ደስ ትሰኛለች። እግሩ በተቀደሰችው ሥፍራ ትመላለሳለች። ጀሮው ለነብስ የተስማማውን ድምፅ ትሰማለች። አፍንጫው ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀውን ማዕዛ ታሸትታለች።
ቤተክርስቲያኗ ከእደሜ ብዛት የተነሳ እድሳት እንደሚሻትም አባ ሃይማኖት ነግረውኛል። ኢትዮጵያውያን ቤተክርስቲያኗ ተጠብቃ እንድትኖር ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። እኔስ በመልካሟ ምድር ድንቅ ነገርን አየሁ። ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀውን ማዕዛ አሸተትኩ። በተቀደሰችው ምድር ተመላለስኩ። መልካሙን ድምፅ አደመጥኩ። የተቀደሰችውን ቤተ መቅደስ በእጄ ዳበስኩ። ሂዱ ወደ ሊቃውንት መገኛ። ወደ ደጋጎች መማፀኛ። የቀደመችውን፣ ያለችውን፣ የምትኖረውን ኢትዮጵያን ታዩባታላችሁ። የከበረውን ታሪክ ትማሩበታላችሁ።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!